ዲፕሎማቶች እና በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ተቀጣሪዎች የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ ሊፈቀድ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያገኙ በርካታ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሬያቸው የሚንቀሳቀሰው ከኢትዮጵያ ውጭ ነው
የውጭ ምንዛሪ አካውንት ለመክፈት የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን ብሔራዊ ባንክ ገልጿል
ዲፕሎማቶች እና በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ተቀጣሪዎች የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ ሊፈቀድ ነው
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቶች ፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ተቋማትንኢኢ ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ እና በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ኢትዮጵያውያን እና የውጭ ዜጎች እንዲሁም ዳያስፖራዎች የውጭ ምንዛሪ አካውንት እንዲከፍቱ የሚያስችል መመሪያ መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታውቋል፡፡
የባንኩ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የሩብ ዓመት አፈጻጸምን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ፣ መመሪያው በቅርቡ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው በተለያዩ ተቋማት እየሰሩ በውጭ ምንዛሬ ገቢ (ደሞዝ) የሚያገኙግለሰቦች በውጭ ምንዛሪ አካውንት (የባንክ ደብተር) ገንዘባቸውን እንዲያስቀምጡ ይደረጋል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ የብዙ ዲፕሎማቶች እና በውጭ ምንዛሪ የሚከፈላቸው ተቀጣሪዎች መቀመጫ ሆና ሳለ የውጭ ምንዛሪያቸው ግን እዚህ ባለመሆኑ እንደሆነ ነው ዶ/ር ይናገር የገለጹት። ለመብራት ፣ ውሃ እና መሰል ክፍያ ካልሆነ በስተቀር ምንም የውጭ ምንዛሬ አያስገቡም ነበር ነው ያሉት ዶ/ር ይናገር፡፡
በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ አካውንት መክፈት ስለማይችሉ ፣ ዲፕሎማቶች እና ሌሎችም በኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ የውጭ ሀገራት ገንዘብ ተከፋይ ግለሰቦች የውጭ ምንዛሪያቸውን ኬንያን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያዩ ሀገራት በሚከፍቱት የውጭ ምንዛሪ አካውንት ነው የሚያንቀሳቅሱት፡፡