የብር ቅያሪ ከተጀመረ ወዲህ 31 ቢሊዮን ብር በአዳዲስ አካውንቶች ወደ ባንክ ገብቷል
በብር ላይ ምንም አይነት ጽሁፍ መጻፍም ሆነ ምልክት ማድረግ በህግ መከልከሉም ተገልጿል
ሀሰተኛ የብር ኖቶች ገበያ ላይ እየታዩ መሆኑን የብሔራዊ ባንክ ገዥ አስታውቀዋል
የብር ቅያሪ ከተጀመረ ወዲህ 31 ቢሊዮን ብር በአዳዲስ አካውንቶች ወደ ባንክ ገብቷል
በመንግስት እና በግል ባንኮች የብር ቅያሪ ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት 26 ቀናት ውስጥ 920 ሺ ገደማ አዳዲስ አካውንቶች መከፈታቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ይናገር ከኢቲቪ ጋር በቀጥታ ስርጭት ባደረጉት ቆይታ አዲስ በተከፈቱት አካውንቶች 31 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ የመቀየሪያ ጊዜው እስከሚጠናቀቅ በርካታ ባንክ የማይጠቀሙ ሰዎች አካውንት እንደሚከፍቱ እና ከባንክ ዉጭ የሚገኝ ገንዘብ ወደባንክ እንደሚመጣም ዶ/ር ይናገር አብራርተዋል፡፡
90 ቢሊዮን አዲሱ የብር ኖት ለባንኮች መሰራጨቱንም ነው የገለጹት፡፡
ከ100ሺህ-1.5 ሚሊዮን ብር ለመቀየር ከተሰጠው የ 1 ወር ጊዜ ውስጥ የቀረው 4 ቀን ብቻ መሆኑን በማስታወስ የተጠቀሰውን ያህል ገንዘብ በእጁ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ግለሰብም ይሁን ድርጅት በነዚህ ጥቂት ቀናት ገንዘቡን ሊቀይር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
የብር ቅያሪው በመላው ሀገሪቱ በአብዛኛው “በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል” ያሉት ዶ/ር ይናገር በአንድ አንድ ቦታዎች “ሀሰተኛ የብር ኖቶች ገበያ ላይ እየታዩ ነው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሀሰተኛ የብር ኖቶች በገበያው ላይ መሰራጨት ኢኮኖሚውን ስለሚጎዳ የጸጥታ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ እና ህብረተሰቡም ይህን ለመከላከል የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ይናገር እንደተናገሩት ከውጭ ሀገራት የኢትዮጵያ ብር አለን በኤምባሲ በኩል እንቀይር የሚል በርካታ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ወደ ውጭ የሚወጣ ሰው ይዞ እንዲወጣ “ከሚፈቀደው የብር መጠን በላይ በ ውጭ ሀገር የኢትዮጵያ ብር ምንም አይሰራም ፤ ይህንን አንቀይርም” ነው ያሉት ዶ/ር ይናገር፡፡ በተለየ ሁኔታ ሊታዩ የሚችሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን የብራዊ ባንክ ገዢው አንስተዋል፡፡
ከባንክ ብር በፈለጉት መጠን ማውጣትን የሚከለክል ህግ ያስፈለገው በዚህ የሚሰራ ወንጀልንም ለመከላከል እንደሆነ በመጥቀስ በቀን በግለሰብ ደረጃ 50 ሺ ብር በተቋም ደግሞ 75 ሺ ብር ብቻ እንዲወጣ የተወሰነውም በጥሬ የሚወጣውን የብር መጠን ለመገደብ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
ከዚህ በፊት ከነበረው መጠን የአሁኑ የቀነሰው በተለያዩ ባንኮች አካውንት በከፈቱ ግለሰቦች “አዲሱም ገንዘብ በብዛት እየወጣ ስለሆነ ነው” ብለዋል፡፡
ገንዘብ ላይ ምንም አይነት ጽሁፍ መጻፍ እና የተለያየ ምልክት ማድረግ በህግ የተከለከለ እንደሆነ እና ለዚህም መመሪያ መዘጋጀቱንም ነው ዶ/ር ይናገር የተናገሩት፡፡