ስለ ኃላፊው ገዳዮች ማንነት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም
ስለ ኃላፊው ገዳዮች ማንነት እስካሁን የታወቀ ነገር የለም
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የባምባሲ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን፣ባህል እና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አውድ መሀመድ ተገደሉ፡፡
አቶ አውድ ባሳለፍነው እሁድ (የትንሳዔ በዓል እለት) ሚያዚያ 11 ቀን 2012 ዓ/ም ነው ከቀኑ 10:00 ሰዓት ላይ ቦሽማ ቀርገጌ በተባለ ቦታ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቀ ታጣቂዎች የተገደሉት፡፡
ኃላፊው በሰርግ እጀባ ስነ ስርዓት ላይ እንደነበሩና ሙሽሮችን አጅበው ከቤጊ ወደ ባምባሲ በመምጣት ላይ ሳሉ መገደላቸውን መረጃውን ለአል ዐይን ያደረሱ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ ኃላፊው በሞተር ሳይክል ወደ ባምባሲ ከተማ ይጓዙ እንደነበር የገለጹት የመረጃ ምንጮቹ ገዳይ ታጣቂዎቹ ምናልባትም የኦነግ ሸኔ አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የታጣቂ ቡድኑ አባላት ከአሁን በፊትም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ ነበር ያሉም ሲሆን ከዚሁ ኃላፊው ከተገደሉበት ቦሽማ ቀርገጌ ቀበሌ 9 ክላሽንኮቭ ጦር መሳሪያዎችን መውሰዳቸውንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱላሂ መሀመድ ኃላፊው መገደላቸውን አረጋግጠውልናል፡፡
ጸረ ሰላም ያሏቸው ኃይሎች “መንግስት ላይ ማድረግ የሚፈልጉትን በአመራሩ ላይ እያደረጉ ነው” ሲሉም ነው አቶ አብዱላሂ የገለጹልን፡፡
የገዳዮች ማንነት ይታወቅ እንደሆነ ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ጉዳዩ ገና በሚመለከታቸው አካላት እየተጣራ ነው” ሲሉ መልሰውልናል፡፡
ገዳዮቹ የኦነግ ሸኔ አባላት ስለመሆናቸው ተጠይቀው “ይሄ ነው ለማለት ይቸግራል፤ ገና እየተጣራ ነው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ሁኔታው ለሌሎች የአስተዳደሩ የአመራር አካላት ስጋትን የሚደቅን እንደሆነ በመጠቆም እየተደረጉ ስላሉ ጥንቃቄዎች ላቀረብንላቸው ጥያቄዎች “ከአሁን ቀደም እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞን አያውቅም፤ ጥንቃቄ መደረግ ግን አለበት፤ ለዚህም እየተሰራ ነው” ብለውናል፡፡
የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ አባላት ግድያው በተፈጸመበት ቦታ እንደሚገኙም ነው ዋና አስተዳዳሪው የነገሩን፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከዞኑ ፖሊስ መምሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ያዕቆብ አልማሙን ስብሰባ ላይ ነኝ በሚል ነው ቆይተን እንድንደውልላቸው የነገሩን፡፡ ሆኖም ስልክ አያነሱም፡፡
“ማንነታቸው የማይታወቅ” ተብለው የሚጠቀሱ አካላት ከአሁን ቀደምም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ከ3 ወራት በፊት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገጹ “ጥር 25/2012 ዓ.ም ማንነታቸው ያልታወቁ አካላት በወረዳው ቦሽማ ቀርኪኪ ቀበሌ ገብተው ነበር” የሚል ዘገባን ራሳቸውን አቶ አብዱላሂን ዋቢ አድርጎ በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስፍሮ ነበር፡፡
“እነዚህ አካላት በዚሁ ቀን ከጧቱ 1፡00 አካባቢ ወደ ቀበሌው ሲገቡ የተደራጀ መረጃ ይዘው እንደነበር ያስታወሱት አስተዳዳሪው፣ ከቀበሌ አመራሮች እና ከሚሊሻ አካላት የጦር መሳሪያ ለመዝረፍ የተለያዩ አስገዳጅ ሙከራ ማድረጋቸውን ነው የገለጹት፡፡
በዚህም በቀበሌው አስተዳዳሪ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን የሚናገሩት አቶ አብዱላሂ፣ በአስተዳዳሪው ላይ መጠነኛ የአካል ጉዳት ያደረሱ ሲሆን፣ ህክምና አግኝተው በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም አመልክተዋል፡፡
የወረዳው አስተዳዳሪ አክለውም፣ የጦር መሳሪያ እና ገንዘብ ለመዝረፍ ባደረጉት ሙከራ 1 የመኖሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን ተናግረዋል” ሲልም ነው ዘገባው የሚያትተው፡፡