ወደ መማር ማስተማር ሂደት ለመመለስ ጥረት ማድረግ መጀመሩን ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ፡፡
በቅርቡ የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል ከተለያዩ አካላት ጋር እየተወያየ መሆኑን ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ይፋ አድርጓል፡፡
ዩኒቨርስቲው እስከመዘጋት ያደረሰውን ሰሞንኛ የጸጥታ ችግር በተመለከተ ከህብረተሰቡ እና ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት እንዲሁም ከሴኔቱ ጋር እየመከረ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደቻሳ ጋንፍሬ ለአል-ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ያቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል የአደጋ ጊዜ ዕቅድ አዘጋጅቶ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዕቅዱ በተማሪዎቹ የሚነሱ የአገልግሎትና ተያያዥ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ትምህርት የሚጀመርበትን ቀን ከማሳወቅ ግን ተቆጥበዋል፡፡
ከጸጥታ ችግሮቹ ጋር በተያያዘ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ አካላትም እንዳሉ ነው ዳይሬክተሩ ያስታወቁት፡፡
ባሳለፍነው ዕሁድ ታህሳስ 18 ቀን 2012 ዓ.ም አንድ የ3ኛ አመት የባንኪንግና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል የዩኒቨርስቲው ተማሪ ከህንጻ ላይ ወድቆ መሞቱ ይታወሳል፡፡ ክስተቱን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲውም የተዘጋው በዚያው እለት ነበር፡፡