ኢትዮጵያ በድርቤ ወልተጂ እና በታደሰ ታከለ ሁለት ተጨማሪ የብር ሜዳሊያዎችን አገኘች
በወንዶች 800 ሜትር የተሳተፈው ዳንኤል ወልዴ ደግሞ 1:48.62 በመግባት 5ኛ ሆኖ አጠናቋል
ድርቤ 4:16.39 በመግባት ነው ለኢትዮጵያ 6ኛውን ብር ያስገኘችው
በመካሄድ ላይ ባለው 18ኛው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያ በድርቤ ወልተጂ እና በታደሰ ታከለ ሁለት ተጨማሪ የብር ሜዳሊያዎችን አገኘች፡፡
ድርቤ በሴቶች 1 ሺ 500 ሜትር 2ኛ ሆና 4:16.39 በመግባት ነው ለኢትዮጵያ 5ኛውን የብር ሜዳሊያ ያስገኘችው፡፡
በተመሳሳይ መልኩ በወንዶች 3 ሺ ሜትር መሰናክል 2ኛ የወጣው ታደሰ ታከለ የብር ሜዳሊያን ሲያስገኝ ሳሙኤል ፍሬው ደግሞ 4ኛ ወጥቷል፡፡
በወንዶች 800 ሜትር የተሳተፈው ዳንኤል ወልዴ ደግሞ 1:48.62 በመግባት 5ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
የ2 ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው ያገኘችው አጠቃላይ የሜዳሊያ ቁጥር 10 ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 2ቱ ወርቅ፣ 6ቱ ብር እና 2ቱ ነሃስ ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡም 6ኛ ላይ ተቀምጣለች፡፡
የወንዶች 800 እና የሴቶች 1 ሺ 500 ሜ አሸናፊ የሆነችው ኬንያ ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡
ሜዳሊያዎቹ በኢማኑዔል ዋኒዮኒ እና ፒዩሪቲ ቼፕኪሩይ የተገኙ ናቸው፡፡
ሌላኛው ሩዲሻ በሚል እየተወደሰ የሚገኘው ኢማኑዔል 800 ሜትሩን 1:43.76 በመግባት የሻምፒዮናውን ሪከርድ ሰዓት አስመዘግቧል፡፡ ፒዩሪቲ ቼፕኪሩይ 1 ሺ 500 ሜትሩን በ4:16.07 ገብታለች፡፡
ድሉ የሻምፒዮናው አዘጋጇ ኬንያ አሁንም በ8 የወርቅ ሜዳሊያዎች ከደረጃ ሰንጠረዡ አናት ተቀምጣ በቀዳሚነት እንድትቀጥል ያስቻለ ነው፡፡
ኬንያ በ3 ሺ ሜትር መሰናክልም 8:30.72 በገባው የ18 ዓመቱ አሞጽ ሴሬም ወርቅ አግኝታለች፡፡