ለታገቱ ተማሪዎች ጉዳይ በም/ጠ ሚኒስትር የሚመራ ኮሚቴ ተቋቋመ እየተከታተለው ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ እና የደኅንነት ኃላፊዎች ልዑክ የታገቱ ተማሪዎችን በተመለከተ በደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ትናንት ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይቷል፡፡
የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ከታገቱት 17 ተማሪዎች መካከል 12ቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መሆናቸውን ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ የአጋቾችን ማንነት፣ ያገቱበትን ምክንያት እና እንዴትና ለምን ታገቱ? የሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ከፍተኛ የምርመራ ቡድን ተዋቅሮ እየተሠራ እንደሆነ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው የገለፁ ሲሆን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ አጣሪ ኮሚቴ ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው ከአሁን በፊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የታገቱት ተማሪዎችን በተመለከተ የተሰጠው መረጃ ትክክል መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
“21 ተማሪዎች መለቀቃቸውን ስንገልጽ የታጋቾቹ ቁጥር በወቅቱ አሁን ከሚባለው በላይ ነበር፤ በዚህ ድርጊት እኛ የቁጥር ጨዋታ ሳይሆን በተጨባጭ ታግተው የነበሩ እና የተለቀቁ ሰዎችን ቁጥር ነው ያሳወቅነው፤ እየሠራን ያለነውም እንደ መንግሥት ኃላፊ ብቻ ሳይሆን እንደ ታጋች ቤተሰብ ሆነን ነው” ብለዋል አቶ ንጉሱ፡፡ ቀሪ የታገቱ ሰዎችን ለማስለቀቅም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአካባቢው ባለሀብቶችን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦች ላይም እገታ እየተፈጸመባቸው እንደሆነ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ምንጭ፡-አብመድ