ወትሮውን በጥላቻ የሚታወቁት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የጋራ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ተስማሙ፡፡
በኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ መሪዎች መካከል ዛሬ ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም በአስመራ በተካሄደው ውይይት፣ መስከረም 2011 ዓ.ም የፈረሙትን የሦስትዮሽ ስምምነት ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የስምምነቱን አፈጻጸም ከመገምገም ባለፈም ለ2012 እና ቀጣይ ዓመታት የጋራ የሽብር ስጋቶችን ለመቀልበስ፣ የሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የመሣሪያ እንዲሁም የአደንዛዥ ዕጽ ዝውውርን ለመግታት የሚሆን የትግበራ ዕቅድ አውጥተዋል።
ቀጣናዊ ትብብርን ለማጎልበትም መሪዎቹ በጋራ ለመስራት ከስምምነት እንደደረሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም፣ ሦስቱ መሪዎች ሀገራቶቻቸው ያሏቸውን የሰው እና የተፈጥሮ ሀብቶች ጥቅም ላይ በማዋል፣ የጋራ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን መስማማታቸው ነው የተገለጸው፡፡
ውጤታማ ትብብር በማድረግ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የሁሉም ህዝቦች የሰላም፣ ደህንነትና ልማት ፍላጎት የተረጋገጠበት እንዲሆን ለማድረግ ከወዳጅና አጋር ሀገራት ጋር የጋራ ጥቅምን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በቅርበት ለመስራትም መሪዎቹ ተስማምተዋል፡፡
ድርቀ፣ ጦርነት፣ ሽብር፣ የመልካም አስተዳደር እጦት እና መሰል ችግሮች የዘመናት መገለጫቸው የሆነው የቀጣናው ሀገራት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተሸለ የትብብር አዝማሚያ በማሳየት ላይ ናቸው፡፡
መልካም የሚባል የህዝብ ለህዝብና የመንግስት ለመንግስት ግንኙነቶችም እየተስተዋሉ ይገኛል፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ መሪነት መምጣት በዚህ ረገድ አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለማሸነፋቸውም አንዱና ዋነኛው ምክኒያት በቀጣናው ሀገራት መካከል ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር ጥረት ማድረጋቸው ነው፡፡
የተለያዩ ለጋሽ ሀገራት እና ድርጅቶች በዚህ ረገድ ድጋፍ የማድረግ ዝንባሌ ማሳየታቸውም ለቀጣናው አንድ ትልቅ ተስፋ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ሀገራቱ ካለባቸው የተለያየ ውስጣዊ ችግር ትብብራቸውን በማጠናከር ቀጣናውን ወደ የተስፋ ምድር ለማድረግ በሚደረገው ጥረት አንዱ ከፍተኛ መሰናክል እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የየሀገራቱ የተለያየ ፍላጎት እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ወትሮውንም ስምምነታቸውን ለማክበር ያላቸው ቁርጠኝነት አናሳ መሆን ሌላው መሰናክል ነው፡፡
ቀጣናው ጠንካራ የሚባልና በሰው ኃይል፣ በቁሳቁስ እንዲሁም በገንዘብ አቅሙ ራሱን ችሎ የሚቆም የጋራ ተቋም የለውም፡፡
ሽብርተኝነትና መሰል የጋራ ችግሮች እንዲሁም ከቀጣናው አጋሮች የፍላጎት ልዩነት ጋር ተያይዞ የሚኖር ተጽእኖ፣ የተለያዩ ሀያላን ሀገራት በቀጣናው ካላቸው ሽኩቻ ጋር ተዳምሮ ምናልባትም የአፍሪካ ቀንድ ማየት የጀመረውን የተስፋ ጭላንጭል እንዳያደበዝዙት ያሰጋል፡፡
በመሆኑም ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮችና ፍላጎቶች በማስታረቅ በጠንካራ የትብብር መንፈስ መስራት ከቀጣናው ሀገራት መንግስታት የግድ ይጠበቃል፡፡