“ሴቶቻችንን መልሱ“ የሚል የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ተበራክቷል፡፡
ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ከደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወጥተው ወደ ቤተሰብ ሲሄዱ ታግተው የተወሰዱ ሴት ተማሪዎች ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ “ሴቶቻችንን መልሱ“ የሚል ሰፊ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻም እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ዘመቻው በዋናነት ለሴት ተማሪዎች ቢሆንም ከታጋቾቹ መካካል ወንድ ተማሪዎች እንደሚገኑበትም ተነግሯል፡፡
ተማሪዎች ከታገቱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ሲሆን እስካሁን የት እንዳሉ፣ በማን እንደታገቱና ያሉበት ሁኔታ በግልጽ ባለመታወቁ ምክንያት የተማሪዎቹን ወላጆች ለከፍተኛ ጭንቀት ዳርጓል፡፡
የአማራ ክልል መንግስት ደብዛቸው የጠፋው የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ እንደሚያሳስበው ገልጿል፡፡
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ላቀ አያሌው ከአብመድ ጋር ባደረጉጽ ቆይታ እንደተናገሩት “ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ“ እና የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድሩ “እንደ ሀገር ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት አናሳ በመሆኑ ፈጥኖ መፍትሔ ማግኘት አልተቻለም” ሲሉም ተናገረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ከሁለት ሳምንታት በፊት ጥር 2 ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እርሳቸው ታገቱ ካሏቸው 27 ተማሪዎች 21ዱ ተለቀዋል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የታገቱ ተማሪዎችን በሰላማዊ መንገድ ለማስለቀቅ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ከአካባቢው ወጣቶች እና መከላከያ ሰራዊት ጋር በተደረገ ጥረት ከታጋቾቹ 21ዱ በሰላም መለቀቃቸውን ተናግረው የነበሩት አቶ ንጉሱ ከነዚህም 13ቱ ሴቶች ሲሆኑ 8ቱ ወንዶች መናቸውን በወቅቱ ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ እስካሁን ተለቀቁ ስለተባሉት ተማሪዎች ምንም መረጃ የለም፡፡
መንግስትም ስለተማሪዎቹ በተለያየ መንገድ ለሚነሳለት ጥያቄ ምንም ምላሽ ሳይሰጥ እስካሁን ዝምታን መምረጡ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡