ኢትዮጵያ እና ሱዳን በድንበር ማህበረሰቦቻቸው ደህንነት እና ሌሎች የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ፡፡
በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ሽፈራው ጃርሶ ከሱዳን መከላከያ ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ጀማለዲን ዑመር ጋር በሁለቱ ሀገራት የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ጥር 11 ቀን 2012 ዓ.ም በካርቱም ተወያይተዋል፡፡
በዚህ ወቅት ሌ/ጄነራል ጀማለዲን ዑመር፣ የኢትዮጵያና የሱዳን ግንኙነት ዘላቂ መሰረት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ሁለቱ ሀገራት ትብብራቸውን ይበልጥ በማጠናከር ለጋራ ጥቅም ማዋል እንዳለባቸውም ነው ሌተናንት ጄነራል ጀማለዲን ዑመር ያነሱት፡፡
የሱዳን ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በውይይታቸው የሁለቱን ሀገራት ድንበር ሰላም ማስከበር እንዲሁም በድንበር ላይ የሚኖሩ የሁለቱን ሀገራት ማህበረሰቦች ደህንነት ማስጠበቅ በሚቻልበት ጉዳይ ላይም ሁለቱ አካላት ተወያይተዋል፡፡ በአስቸኳይ ጥምር ሀይል በማቋቋም ህገወጥ ዝውውር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ ለመስራት መስማማታቸውም ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በሱዳን የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖር እንደምትፈልግና ለዚህም ቁርጠኛ ድጋፍ እንደምታደርግ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ስም ከሽብርተኝነት ዝርዝር ውስጥ እንዲፋቅ ኢትዮጵያ የራሷን ሚና እንደምትወጣም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት በማስቀጠል በድንበር በኩል የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማድነቅ፣ በሀገራቱ ተቀባይነት ያለው ድንበር ተሸጋሪ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠር የድንበር አካባቢ ችግሮችን ለመፍታት አስተዋጽኦው የጎላ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮ-ሱዳን የጋራ የድንበር ኮሚሽን ተጠናክሮ መከላከያ ሚኒስትሮችን ያካተተ እንዲሆንም በውይይቱ መነሳቱን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ምንጭ፡- የሱዳን ዜና አገልግሎት