“እኛ እናልቃለን ብለን በፍርሃት ስንሸሽ ነበር፤አላጠናንም“-የመተከል ተፈታኞች
በመተከል የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች የሥነ ልቦና ዝግጅት አላደረግንም ብለዋል
ከፈተና ጋር ተያይዞ ለ“ታዳጊ ክልሎች” ሲደረጉ የነበሩት ማበረታቻዎች ይቀጥላሉ ተብሏል
በቀጣይ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በሚደረገው ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ ለመቀመጥ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዳላደረጉ በመተከል የ 12 ኛ ክፍል ተፈታኞች ገለጹ፡፡
ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተማሪዎች በመተከል ውስጥ በነበረው ጭፍጨፋ ምክንያት በህይወት ለመኖር እንጅ ፈተና ላይ ለመቀመጥ እንዳላሰቡ ገልጸዋል፡፡በአካባቢው ማንነትን መሰረት ባደረገው ግድያ ምክንያት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ህይወትን ለማዳን በሚል ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲዘዋወሩ እንደነበርም ነው የገለጹት፡፡
ከአስተያየት ሰጭዎች መካከል ስሙን መጥቀስ ያልፈለገ በወንበራ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ የሆነው “እኛ እናልቃለን ብለን በፍርሃት ስንሸሽ ነበር፤ ምንም ነገር አላጠናንም“ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ለዚህ ጉዳይ እልባት ሊሰጠው እንደሚገባ ተማሪው ጠይቋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጭ ተማሪ ድሪባ ተስፋዬ በበኩሉ አሁን ላይ በርካቶች ተፈናቅለው እንዳሉ ገልጾ ለፈተና ዝግጅት እንዳላደረጉ ተናግሯል፡፡ አሁን ላይ በመተከል ዞን የሚገኙ ተፈታኞች “መንግስት ምን ያህል ለእኛ ይጨነቃል፤ ምን ያህል ያስብልናል የሚል ጥያቄ አለን“ ብለዋል ተማሪዎቹ፡፡
ምንም እንኳን ፈተናው ከዚህ የበለጠ ቢራዘም በተማሪዎች ላይ ሌላ ጭንቀት እንደሚያመጣባቸው ያነሱት ተማሪዎቹ በመተከል ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት የትምህርት ሚኒስቴር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
ሀገር ዓቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ በበኩሉ ቀደም ሲል ለ“ታዳጊ ክልሎች” ሲደረጉ የነበሩ ማበረታዎች እንደሚቀጥሉ ገልጿል፡፡ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲላሞ ኦቶሬ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ የፊታችን የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም ሊሰጥ የታቀደው ፈተና በሀገሪቱ ሁሉም ቦታዎች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አስተያየት ሰጭ ተማሪዎች ከፈተና በኋላ የማለፊያ ነጥብ ሲወሰን መንግስት የመተከልን ሁኔታ ከግምት እንዲያስገባ መጠየቃቸውን አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ዳይሬክተሩ አሁን የኤጀንሲው ስራ ፈተና መፈተን መሆኑን አንስተው ውጤት የሚወሰነው በበላይ አካላትና ተቋማት ነው ብለዋል፡፡
ይሁንና ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን በተመለከተ ቀደም ሲል ለ “ታዳጊ ክልሎች” ሲደረግ የነበረው ማበረታቻ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የመተከል ዞን የዚህ ማበረታቻ ተጠቃሚ በመሆኑ ጉዳዩ በዚህ እንደሚታይ አንስተዋል፡፡በበርካታ ግድያዎች ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ ካለው መተከል አካባቢ የተነሳው የተማሪዎቹ ቅሬታና አስተያየት ትክክለኛ መሆኑንም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ይህ ችግርና ቅሬታ ከፈተና በኋላ ሊታይ እንደሚችልም ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡