መንግስት የቤንሻንጉል ተጎጂዎችን እንዲክስና ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ኢሰመጉ አሳሰበ
ከጳጉሜ ጀምሮ በመተከል እና በዳንጉር የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች የበርካታ ንጹኃን ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን አስታውቋል
ጉባዔው የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበርም ጠይቋል
መንግስት የቤንሻንጉል ተጎጂዎችን እንዲክስና ጥፋተኞች እንዲጠየቁ ኢሰመጉ አሳሰበ
የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) መንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህነነትና ነጻነት የመጠበቅ መብትን እንዲያስጠብቅ አሳሰበ፡፡
ጉባዔው ከጳጉሜ ወር ጀምሮ ማንነቸታው ባልታወቁ አካላት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞንና በዳንጉር ወረዳ የተለያዩ አካባቢዎች የበርካታ ንጹኃን ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን ዛሬ ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጥቃቱ እየደረሰባቸው ያሉ ወረዳዎች በኮማንድ ፖስት ሥር ሆነው የጸጥታ ማስከበር እርምጃዎች እየተሰሩ ቢሆንም አሁንም ተጨባጭ ስጋቶች አሉ ያለው ጉባዔው ከአሁን ቀደም እንዳሳሰበው ሁሉ መንግስት በአካባቢዎቹ የሚፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በከፍተኛ ትኩረት እንዲመለከትና የሰዎችን በህይወት እና በሰላም የመኖር፣የአካል ደህንነትና ነጻነት የመጠበቅ መብትን በሙሉ እንዲያስጠብቅ አሳስቧል፡፡
የጥቃቱ ተሳታፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የጠየቀም ሲሆን ለተጎጂዎች ተገቢው ካሳ እንዲሰጥና የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማጣራት የሚቻልበትን ሁኔታ እንዲመቻች ጠይቋል፡፡
ጉባዔው አያይዞም ከመስከረም 11 እስከ 14 ቀን 2013 ዓ/ም ድረስ ባሉት ቀናት መነሻቸውን ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች አድርገው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ወደ ከተማው እንዳይገቡ በመደረጋቸው ዜጎች ለእንግልትና ለተለያዩ ወጪዎች መዳረጋቸውን ገልጿል፡፡
በመሆኑም የዜጎች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት እንዲከበር እና የዜጎችን መብት የሚገድቡ መንገድ መዝጋትና መሰል እንቅስቃሴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ጠይቋል፡፡