የጂቡቲው መሀሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበርነት ምርጫን አሸነፉ
መሀሙድ አሊ የሱፍ 33 ድምጽ ሲያገኙ ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ 21 ድምጽ አግኝተዋል

ተፎካሪዎች አሸናፊ የሚያደርጋቸውን 32 ድምጽ ማገኝት ባለመቻላቸው አሸናፊውን ለመለየት 7 ዙር ድምጽ ተሰጥቷል
የጂቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀሙድ አሊ የሱፍ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበርነት ምርጫን አሸነፉ።
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ "የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን" በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ጉባዔው በመጀመሪያ ቀን ውሎው ህብረቱን ኮሚሽን ለቀጣይ አራት ዓመታት የሚመሩትን ሊቀመንበር ምርጫን አካሂዷል።
በዚህም ጂቡቲን ወክለው በእጩነት የቀረቡት መሀሙድ አሊ የሱፍ ምርጫውን በማሸነፍ ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር በመሆን መመረጣቸውን አል ዐይን አማርኛ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በምርጫውም መሀሙድ አሊ የሱፍ 33 ድምጽ ሲያገኙ ከፍተኛ የማሸነፍ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት ዋነኛ ተቀናቃኛቸው የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ 21 ድምጽ አግኝተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ለመሆን የሚያበቃውን ድል ለመቀዳጀት ተፎካካሪዎች 32 ድምጽ ማገኘት ይጠበቅባቸዋል።
ተፎካካሪዎች አሸናፊ የሚያደርጋውን 32 ድምጽ ማገኝት ባለመቻላቸው አሸናፊውን ለመለየት 7 ዙር ድምጽ ተሰጥቷል።
በመጨረሻም የጂቡቲው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀሙድ አሊ የሱፍ 33 ድምጽ በማግኘት ቀጣዩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚን ሊቀ መንበር መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ላለፉት 8 ዓመታት የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ መሃማት የስልጣን ዘመንም ተጠናቋል፡፡