የአፍሪካ መሪዎች በቅኝ ግዛት ጊዜ ለተፈጸሙ በደሎች ካሳ እንዲከፈል ሊጠይቁ ነው
መሪዎቹ በኢትዮጵያ በሚያካሄዱት 38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ በጉዳዩ ላይ እንደሚወያዩ ተነግሯል
![](https://cdn.al-ain.com/images/2025/2/13/273-162658-whatsapp-image-2025-02-13-at-11.17.59-am_700x400.jpeg)
ከ15ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ 12.5 ሚሊየን አፍሪካውን በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት በባሪያ ንግድ ቀርበዋል
የአፍሪካ መሪዎች በቅኝ ግዛት ዘመን እና በባሪያ ንግድ ለተፈጸሙ በደሎች ካሳ እንዲከፈል ግፊት ሊያደርጉ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
መሪዎቹ በወቅቱ ለተፈጸሙ ታሪካዊ ስህተቶች እና በደሎች ምዕራባውን ቅኝ ገዢዎች ካሳ እንዲከፍሉ የሚጠይቀውን ሀሳብ እንደሚወያዩበት ተነግሯል፡፡
ኢፍትሀዊነትን የሚያራምዱ አለም አቀፋዊ ፖሊሲዎች ለውጥ እንዲደረግ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የመሳሰሉ አለምአቀፋዊ ተቋማት ቅኝ ገዢዎች በወቅቱ ለፈጸሟቸው ስህተቶች ተጠያቂ እንዲሆኑ ግፊት እንዲያደርጉ ጥያቄ እንደሚቀርብም ነው የተገለጸው፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ አጀንዳው ለውይይት ሊቀርብ እንደሚችል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በጉባኤው ላይ መሪዎች የካሳ ሂደቱ የገንዘብ ክፍያ እና ለታሪካዊ ጥፋቶች እውቅና መስጠትን እንዲያካትት በሚጠይቅ እቅድ ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡
በጉዳዩ ላይ በአባል ሀገራት ዘንድ ሲመክርበት እንደቆየ ይፋ ያደረገው የአፍሪካ ህብረት የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና የባህል ምክር ቤት፤ በካሳ ላይ የሚካሄደው ክርክር ቅኝ አገዛዝ እና ባርነት ከዘረኝነት ጀምሮ በአፍሪካ እና በበለጸጉ ምዕራባውያን ሀገራት መካከል ያስከተለውን የኢኮኖሚ ልዩነት ማረም ላይ ትኩረቱን እንዳደረገ ገልጿል፡፡
ከዚህ ባለፈም በቅኝ ገዢዎች የተወሰዱ ቅርሶች እንዲመለሱ እና ከቅኝ ግዛት በፊት የነበሩ ቦታዎች ወደ ቀደመ ይዞታቸው እንዲመለሱ ሊጠይቅ እንደሚችልም ነው የተነገረው፡
የካሳ ጥያቄው በይፋ ከመቅርቡ በፊት ከተለያዩ ቀኝ ዘመም ምዕራባውን ሀገራት መሪዎች ተቃውሞ እየገጠመው እንደሚገኝ የጠቀሰው የሮይተርስ ዘገባ የመሳካት እድሉ ጠባብ መሆኑን አመላክቷል፡፡
በብሪታንያ የቀኝ ዘመም ፓርቲ መሪው ኒጄል ፍራጅ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በካሳ ክፍያ ጉዳይ ለውይይት የሚቀመጡ ከሆነ “ደካማ መሆናቸውን” በግልጽ ያሳያሉ ብለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በበኩላቸው ከካሳ ክፍያ ይልቅ የእርቅ ሂደት እንዲከናወን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ጉዳዩን ከተቃወሙ ሀገራት መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው የካሳ ትግበራው እውናዊነት እንደማይታቸው እና ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በቅኝ ግዛት ለተፈጸሙ በደሎች ካሳ እና እውቅና እንዲሰጥ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ቢያደርግም እምብዛም ፍሬያማ ውጤት አለማስመዝገቡን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከ15ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን 12.5ሚሊየን አፍሪካውያን በግዳጅ ታፍነው በአውሮፓ ነጋዴዎች በባርነት ገበያ መቅርባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡