ለቀልድ ተብሎ የተደረገው የዘረመል ምርመራ ፍጹም ያልተጠበቀ ውጤት አምጥቷል
የ20 አመቷ እንግሊዛዊት ያደረገችው ምርመራ አጎቷ ወላጅ አባቷ መሆኑን አሳይቷል
ከሟች ሚስቱ የወለዳት ብቸኛ ልጅ እንደሆነች አምኖ ለ20 አመታት የኖረው አባት በገዛ ወንድሙ በተፈጸመበት ክህደት በልብ ስብራት ውስጥ ይገኛል
የ20 አመቷ እንግሊዛዊት ለቀልድ በሚል ባደረገችው የዲኤንኤ (ዘረመል) ምርመራ ወላጅ አባቷ አጎቷ መሆኑን አውቃለች፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው ለ20 አመታት ያሳደጋት አባቷ ለልደቱ የቤት ውስጥ የዴኤንኤ መመርመሪያ ኪት ይሰጠዋል፤ አጋጣሚውን ተጠቅመን ዘረመላችን ምን ያህል እንደሚመሳሰል እንወቅ በሚል ተስማምተው ምርመራውን ያደረጉት አባት እና ልጅ በውጤቱ ልባቸው ተሰብሯል፡፡
ወደ ሆስፒታል የተላከው የዘረመል ናሙና ከአምስት ሳምንታት በኋላ ውጤቱ ሲመጣ አባት እና ልጅ ተባብለው ለ20 አመታት በአንድ ቤት ውስጥ የኖሩት ሰዎች ናሙና ፍጹም የተለያየ ሆኖ ይገኛል፤ በሁኔታው ተደናግረው ወደ ሆስፒታል በመሄድ በድጋሚ ምርመራ ያደረገችው ወጣቷ ዲኤንኤዋ ከአባቷ ይልቅ ከአጎቷ ጋር እንደሚመሳሰል አውቃለች፡፡
ከመኖርያ ቤታቸው በቅርብ ርቀት ላይ የሚኖረው ወላጅ አባቷ ሆኖ የተገኘው የአባቷ ወንድም በተደጋጋሚ ወደቤታቸው አባቷ በሌለበት ይመጣ እንደነበር ነገር ግን ከሟች እናቷ ጋር ድብቅ የፍቅር ግንኙነት እንደነበራቸው ጠርጥራ እንደማታውቅ ተናግራለች፡፡
እናቷ ባጋጠማት የጤና እክል በልጅነቷ እንደሞተች የምትናገረው ወጣቷ አባቷ ብቻውን ስላሳደጋት ያላቸው ቅርርብ እና ወዳጅነት ከፍተኛ እንደሆነ ታሪኳን በጋራችበት ሪድኢት በተሰኘው ማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ አስፍራለች፡፡
“ህይወቴን የሚገለባብጥ ሁኔታ ለቀልድ ባደረኩት ነገር ይፈጠራል ብየ አላሰብኩም፤ ወላጅ አባቴ ሆኖ የተገኘው አጎቴ ስለጉዳዩ የሚያውቀው ነገር እንዳለ መጠየቅ እንዳለብኝ እና እንደሌለብኝ ግራ ተጋብቻለሁ ስትል” ነው ታሪኳን ያጋራችው፡፡
የሚስቱን ሞት ተከትሎ ብቸኛ ልጁ እንደሆነች አስቦ ለብቻው ያሰደገው አባት ሁኔታው ሊቀበለው ከሚችለው በላይ በመሆኑ ግራ ተጋብቶ በሀዘን ውስጥ ይገኛል ፡፡
ያሳደጋት አባቷን በምን አይነት መንገድ እንደምታረጋገው እና ወደቀደመ ህይወታቸው እንዴት መመለስ እንደሚችሉ በጽሁፏ የጠየቀችው እንግሊዛዊት ወጣት በርካታ ግብረ መልሶችን አግኝታለች፡፡
ብዙዎች የምርመራ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን በአሳዳጊ አባቷ እና በእርሷ መካከል ያለውን ቤተሰባዊ ፍቅር እንደማይለውጠው እና ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍቅር እና እንክብካቤ እንድትሰጠው ሲመክሯት፤
ሌሎች ደግሞ ለአባቷ የቤት ውስጥ የዲኤንኤ መመርመሪያ መሳርያ በስጦታነት የሰጡት ሰዎች የሚያውቁት ነገር ሊኖር ስለሚችል ተጨማሪ ማጣራቶችን እንድታደርግ መክረዋታል፡፡
ጉዳዩን ይዞት የወጣው ሚረር ጋዜጣ የዜናውን እውነተኛነት ከባለታሪኳ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡