ከአባት እና ልጅ በተለገሰ የወንድ የዘር ፍሬ የተወለደ ህጻን ትክክለኛ አባቱ ማን ሆናል?
ከአምስት ዓመት በፊት ከአባት እና ልጅ በተለገሰ የወንድ የዘር ፍሬ የተወለደው ልጅ ትክክለኛውን አባት ማግኘት አልቻለም
የአባትነት ማስረጃ ለማግኘት ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ቢያመራም ችሎቱ ህጻኑ አባት እና አያት አልባ ነው ሲል ወስኗል
በብሪታንያ ከአባት እና ልጅ በተለገሰ የወንድ የዘር ፍሬ የተወለደው ህጻን ሚስጢርነቱ እንደጠበቅ ፍርድ ቤት አዘዘ፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በአውሮፓዊቷ ብሪታንያ የተከሰተው አንድ ክስተት አሁንም ማጨቃጨቁን የቀጠለ ሲሆን እልባት እንዲያገኝ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው
በብሪታንያ ሼፊልድ ብራንስሌይ በሚባል ቦታ የሚኖር አንድ ሰው ልጅ መውለድ ይፈልጋል፡፡ አባት መሆን የፈለገው ይህ ስሙ ያልተጠቀሰ ግለሰብ ወደ ህክምና ቦታ ሲያመራ የወንድ ዘር ፍሬው መጠን እና አቅሙ ደካማ እንደሆነ እና እርግዝና እንዲፈጠር የሚያደርግ እንዳልሆነ ይነገረዋል፡፡
የወንድ የዘር ፍሬው የአቅም ማነስ ችግር እንዳለበት የተነገረው ይህ ግለሰብ ከሌላ ወንድ የተወሰነ የዘር ፍሬ ቢሰጠው እርግዝና መፍጠር እንደሚቻል በሐኪሞች ይነገረዋል፡፡
ይህ ግለሰብም በሀኪሞች እርዳታ አማካኝነት የእሱን እና የአባቱን የወንድ የዘር ፍሬ በማደባለቅ በቤተ ሙከራ እገዛ አማካኝነት ወደ ሚስቱ ማህጸን እንዲገባ እና ጽንስ እንዲፈጠር ይደረጋል፡፡
በዚህ የህክምና ዘዴ አማካኝነትም የተጸነሰው ህጻን ከተወለደ አሁን አምስት ዓመት የሆነው ሲሆን ይህ ሰው አባት ስለመሆኑ ማስረጃ ማግኘት አልቻለም፡፡
ከ70 ዓመቷ ሚስቱ መንታ ልጆችን ያገኘው አባት ጠፋ
አባት መሆኑን በፍርድ ቤት ለማስወሰን በሚል ጉዳዩን ወደ ህግ ቦታ እንደወሰደው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ የቀረበለት የብራንስሌይ ፍርድ ቤትም የተፈጸመው የወንድ የዘር ፍሬ ማደባለቅ ትክክል አለመሆኑን፣ አባት ነኝ በሚል የቀረበው ሰውም የህጻኑ ወንድም የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ብሏል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ ምርመራ ቢደረግ አያት ነኝ የሚሉት ግለሰብ የህጻኑ አባት የመሆን እድል አልያም ሌላ የምርመራ ውጤት ሊከሰት ስለሚችል አጨቃጫቂነቱ ይቀጥላል ሲልም ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡
ህጻኑ በዚህ መንገድ መወለድ እንዳልነበረበት ያለው ፍርድ ቤቱ ጉዳዩ በህጻኑ አዕምሮ ላይ ሊያደርሰው የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ሚስጢርነቱ እንዲጠበቅ ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡