ከሆዱ ውስጥ 65 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም በህይወት ያለ አሳ በቀዶ ጥገና የወጣለት ወጣት
የወጣቱን አንጀት እየተመገበ የነበረው አሳ ወደ ወጣቱ ሆድ እቃ ውስጥ እየገባ እንዳለ በተፈጠረበት ህመም ወደ ሆስፒታል ሲሄድ በሰውነቱ ውስጥ አሳ እንደሚገኝ አውቋል
በህይወት ያለው አሳ በምን አይነት መንገድ እንደገባ እና ለምን ያህል ጊዜ በወጣቱ ሆድ ውስጥ እንደቆየ አልታወቀም
ነዋሪነቱን በቬትናም ዋና ከተማ ሃኖይ ያደረገው የ31 አመት ህንዳዊ ወጣት ከሆዱ ውስጥ 65 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም አሳ በቀዶ ጥገኛ ወጥቶለታል፡፡
ስሙ ያልተጠቀሰው ህንዳዊ ወጣት በሆዱ ላይ በተፈጠረበት ከፍተኛ ህመም ወደ ህክምና ያቀናል፡፡
በዛም ከህክምና ባለሙያዎች ጋር በነበረው ቆይታ ሆዱ ውስጥ የሚንቀሳቀስ ነገር እንዳለ ይናገራቸዋል፡፡
ሃኪሞቹ የተለያዩ የህክምና ክትትሎችን እያደረጉ ባሉበት ወቅት የወጣቱ የህመም ስቃይ እየተባባሳ በመምጣቱ በአልትራሳውንድ ያዩት ምስል አስገራሚ ሆኖባቸዋል፡፡
የእባብ ቅርጽ ያለው ኢል የተሰኝው የአሳ ዝርያ በወጣቱ ሆድ ውስጥ እንደሚገኝ የተገነዘቡት ሀኪሞቹ በአፋጣኝ የቀዶ ህክምና በማድረግ 65 ሴንቲ ሜትር የሚረዝመውን እና የዙርያ ስፋቱ 10 ሴንቲ ሜትር የሚለካ በህይወት የሚገኝ አሳ ከወጣቱ ሆድ ውስጥ አውጥተዋል፡፡
ከህክምናው በኋላ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተሮች ከሰዎች ሆድ ውስጥ በርካታ ባዕድ ነገሮችን በቀዶ ጥገና አስወግደናል ይህን ያህል መጠን ያለው በህይወት ያለ አሳ ግን ለመጀመርያ ጊዜ ሲያጋጥመን ነው ብለዋል፡፡
አሳው በምን አይነት መንገድ በወጣቱ ሆድ ውስጥ እንደገባ እርግጠኛ ያልሆኑት ዶክተሮች የአንጀት ክፍሉን ተመግቦ ወደ ሆድ እቃ ውስጥ በመግባት ላይ እንዳለ እንደደረሱበት ተናግረዋል፡፡
አክለውም የሰአታት ልዩነት የታማሚውን ህይወት ሊያሳጣ ይችል እንደነበር እና ቀዶ ጥገና ለማድረግ የደረሱበት ውሳኔ ህይወቱን መታደግ እንደቻለ ነው የገለጹት፡፡
በአሳው ጉዳት የደረሰበትን የአንጀት ክፍል ለመጠገን የህክምና ባለሙያዎቹ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ለከፋ አደጋ የሚሰጥ ጉዳት እንዳልደረሰበት አሳውቀዋል፡፡