በጨዋታው ዋዜማ ዕለት ከመጠን በላይ ጠጥተው የተገኙት ዳኞች በሌሎች ዳኞች ተተክተዋል
ሰክረው የተገኙት የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ዳኞች
ወቅቱ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ላይ የሚሳተፉ 32 ክለቦችን ለመለየት የማጣሪያ ውድድሮች የሚካሄዱበት ነው።
በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የስኮትላንዱ ሬንጀርስ ከሜዳው ውጪ የዩክሬኑን ዳይናሞ ኪቭ ጋር መጫወት ነበረበት።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ መሆኗን ተከትሎ ዳይናሞ ኪቭ ጨዋታውን በፖላንዷ ሉብሊን ከተማ ለማድረግ ይስማማሉ።
አንድ አቻ የተጠናቀቀው ይህ ውድድር በሰከሩት ዳኞች ምትክ ሌሎች ዳኞች ተተክተው ተካሂዷል።
ይህን ጨዋታ ከሚዳኙት መካከል ደግሞ ሁለት የፖላንድ እግር ኳስ ዳኞች በውድድሩ ላይ ከተመደቡት መካከል ዋነኞቹ ናቸው።
የተንቀሳቃሽ ምስል እርዳታ ዳኝነት ወይም የቫር ዳኝነት እንዲሆኑ የተመደቡት እነዚህ ፖላንዳዊያን በጨዋታው ዋዜማ ዕለት ሰክረው ተገኝተዋል።
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ ከሆነ ዳኞቹ ከመጠን በላይ ጠጥተው መንገዶች ዳር የተተከለን የትራፊክ ምልክት ለማስወገድ ሲጥሩ በፖሊስ ተይዘዋል።
የማጣሪያ ውድድሩን ያዘጋጀው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሙያቸውን ባላከበሩት ዳኞች ምትክ ሌሎች ዳኞችን በመመደብ ጨዋታው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ አድርጓል።
የፖላንድ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በዳኞቹ ያልተገባ ድርጊት ማዘኑን ገልጾ ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ዳኞቹ ጥፋተኝነታቸው ከተረጋገጠ እስከወዲያኛው ከውድድር ሊያግድ እንደሚችል አስጠንቅቃል።