ሆስፒታሉ በ2006ቱ የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ወቅት ነበር የተሰራው
በሰሜናዊ እስራኤሏ የወደብ ከተማ ሃይፋ ከምድር በታች የተገናባ ግዙፍ ሆስፒታል አለ።
ከ2 ሺህ በላይ ህሙማንን ማስተናገድ የሚችሉ አልጋዎች ያሉት ግን አንድም ታካሚን የማያስተናግድ።
ራምባም የተሰኘ የህክምና ማዕከል በሃይፋ ይህን የመሬት ውስጥ ሆስፒታል የገነባው በፈረንጆቹ 2006 እስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት ሲጀምሩ ነው።
ይህ ሆስፒታል ከዚህ ጦርነት መደምደም በኋላ አገልግሎት መስጠት ቢያቆምም የህክምና ቁሳቁሶቹም ሆነ አልጋዎቹ በነበሩበት ናቸው።
- ሆስፒታሉ ከባለብዙ ፎቅ ህንጻ ስር የተገነባ ሲሆን፥ አገልግሎት ካቆመ በኋላ የመኪና ማቆሚያ ሆኗል።
የመኪና ማቆሚያውን ወደ ግዙፍ ሆስፒታልነት ለመቀየር ግን ሶስት ቀናት ብቻ በቂ ናቸው ይላል የቢቢሲ ዘገባ።
ሆስፒታሉ ከሃማስ የጥቅምት 7 ጥቃት በኋላ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል።
በተለይ በቴህራን እና ቤሩት የሃማስና ሄዝቦላህ አመራሮች ከተገደሉ በኋላ ኢራን አጻፋዊ እርምጃ እወስዳለሁ ካለች በኋላ ሆስፒታሉ ዝግጁ ሆኖ በተጠንቀቅ እንዲጠባበቅ ታዟል።
ለሊባኖስ ቅርብ የሆነችው ሃይፋ ከሄዝቦላህ ሊሰነዘር የሚችል የሮኬት ጥቃት ያሳስባታል።
“(ጥቃቱ) መቼ ይፈጸማል የሚለውን ማንም አያውቅም፤ ሰዎች እየተጨነቁ ነው” የሚሉት የመሬት ውስጥ ሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር አቪ ዌስማን፥ ወቅታዊው ውጥረት አሳሳቢ መሆኑን ይናገራሉ።
የሃይፋ ነዋሪዎች ለወራት ከሮኬት ጥቃት ለማምለጥ ወደ መደበቂያ ስፍራዎች ሲገቡ ቆይተዋል፤ ተማሪዎችም በየጊዜው ጥቃት ቢፈጸም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲለማመዱ ነው የሚውሉት።
ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገች የከተማዋ ነዋሪ አሁን ያለውን ሁኔታ ስታስረዳ “በስአት የተሞላ ቦምብ ለመፈንዳት የመቃረብ አይነት ነው” ብላለች።
ሃይፋ አይሁዳውያን እና አረቦች ተሰባጥረው እንደሚኖሩባትና በ2006ቱ የእስራኤልና ሄዝቦላህ ጦርነት የጦርነትን ጉዳት በሚገባ ማየቷን የሚያወሱት ደግሞ ወቅታዊው የኢራን እና እስራኤል ፍጥጫ ለዝቦ፤ የጋዛ ጦርነት ቆሞ ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት እንደሚሹ ተናግረዋል።