ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን በሱዳን ሰራተኞቹ ጥቃት እንደደረሰባቸው ተናገረ
በሀገሪቱ ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ለወራት በዘለቀው ጦርነት ብዙዎች ለሰብዓዊ ቀውስ መጋለጣቸው ተነግሯል
ከጥቃቱ ጀርባ የትኛው ተፋላሚ ኃይል እንደሆነ ግልጽ አይደለም
ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የእርዳታ ሰራተኞቹ በሱዳን ዋና ከተማ ለሆስፒታል የህክምና ቁሳቁሶችን ሲያደርሱ በታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው አስታውቋል።
ሀሙስ እለት በዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቱ የሚሰሩ 18 ሰዎች በደቡባዊ ካርቱም ከሚገኝ ሆስፒታል ቁሳቁሶችን ለማምጣት ሲሞክሩ ጥቃት እንደደረሰባቸው የእርዳታ ቡድኑ በመግለጫው ገልጿል።
ከተጠረጠረው ጥቃት ጀርባ የትኛው ተፋላሚ የሱዳን ኃይል እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
"ቡድኑ በስፍራው የተገኘበትን ምክንያት ከጠየቁ በኋላ የታጠቁት ሰዎች በኃይል ደበደቡዋቸው፣ አካላዊ ድብደባ እና ግርፊያ ፈጽመውባቸዋል" ሲል ስለ ድርጊቱ ገልጿል።
"ሹፌሩን አስረው ከመልቀቃቸው በፊት ህይወቱን አስፈራርተው ተሽከርካሪውን ሰርቀዋል" ብሏል።
ቡድኑ ክስተቱ በደቡባዊ ካርቱም ክፍት ከሆኑት ከሁለቱ አንዱ በሆነው ሆስፒታሉ ያለውን እንቅስቃሴ አደጋ ላይ ጥሎታል ብሏል።
የሱዳን ድንበር የለሽ የሀኪሞች ቡድን የድንገተኛ አደጋ ስራ አስኪያጅ ክሪስቶፍ ጋርኒየር "እንዲህ አይነት ክስተት በድጋሚ ቢከሰት እና እቃዎችን የማንቀሳቀስ አቅማችን እየተስተጓጎለ ከቀጠለ በሚያሳዝን ሁኔታ በሆስፒታሉ መገኘታችን ሊጸና የማይችል ይሆናል" ብለዋል ።
ከሚያዝያ ጀምሮ በሱዳን ጦር እና በፈጣኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሰላማዊ ዜጎችን ከዋና ከተማው ማፈናቀል እና በምዕራብ ዳርፉር ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን አስከትሏል።
ወደ ጎረቤት የአፍሪካ ሀገራት ያልተሰደዱ ሰዎች ለከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ተዳርገዋል።