በዱባይ አውሮፕላን ማረፊያዎች አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት ሊጀምሩ ነው
የአነፍናፊ ውሾቹ በኮሮና የተያዘን ሰው የመለየት አቅም 98.2 በመቶ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ነው ተብሏል
አነፍናፊ ውሾቹ ከመንገደኞች የሚወሰድ የላብ ናሙናን በማሽተት ቫይረሱ ያለበትን ሰው ይለያሉ ተብሏል
በዱባይ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ የአየር መንገድ አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ መንገደኞችን መለየት ሊጀምሩ መሆኑ ታውቋል።
የዱባይ ፖሊስ እንዳስታወቀው በልዩ ሁኔታ ስልጠና በወሰዱ የፖሊስ አነፍናፊ ውሾች አማካኝነት በኮቪድ 19 የተያዙ ሰዎች ልየታ በቅርቡ ይጀመራል።
ለኮሮና ምርመራ ልስልጠናው የጀርመን ሺፐርድ ውሻን ጨምሮ በርካታ የውሻ ዝርያ መጠቀሙንም የዱባይ ፖሊስ አስታውቋል።
አነፍናፊ ውሾች በኮሮና የተያዙ ሰዎች ላብ እንዲያሸቱ በማድረግ ቫይረሱን መለየት እንዲችሉ ስልጠና መውሰዳቸውንም ነው ፖሊስ ያስታወቁት።
በዚህም መንገደኞች አሊያም ቫይረሱ አለበት ተብሎ የተጠረጠረ ሰው ፖሊስ የሚሰጠውን የላብ ናሙና መቀበያ በብብቱ ስር ቢበዛ ለ5 ደቂቃ እንዲይዝ ከተደረገ በኋላ ውሻዎቹ ላቡን አሽትተው በግለሰቡ ላይ ቫይረሱ መኖር አለመኖሩን ይለያሉ።
ናሙና የተወሰደለት ሰው ላይ ቫይረሱ ካለ ውሻው በመጮህ ድምጽ የሚያሰማ መሆኑንም ነው የዱባይ ፖሊሶች ያስታወቁት።
አነፍናፊ ውሾቹ በቅርቡ በአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን መለየት እንዲጀምሩ እንደሚደረግም ፖሊሶች ገልጸዋል።
ስልጠና የወሰዱ አነፍናፊ ውሾች ተሰጣቸውን ሳምፕል በማሽተት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን በሰከንዶች ውስጥ መለየት እንደሚችሉም ተረጋግጧል።
አነፍናፊ ውሾች በኮሮና ቫይረስ የተያዘን ሰው የመለየት አቅም 98.2 በመቶ ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ መሆኑንም ነው የገለጹት።