ብሪታኒያ የኮሮና ክትባት የባለቤትነት የፈጠራ መብቶች ይቅሩየሚለውን ሃሳብ ልትደግፍ ትችላለች ተባለ
የፈጠራ ባለቤትነት መብቶቹ እንዲቀሩ የሚያጠይቅ ምክረ ሃሳብ በደቡብ አፍሪካና ህንድ አቅራቢነት ለዓለም የንግድ ድርጅት ገብቷል
ሃሳቡን እንድትደግፍ ጫና እየበረታባት ያለችው ብሪታኒያ በጉዳዩ ላይ በመምከር ላይ መሆኗ ተገልጿል
ብሪታኒያ በዓለም ዙሪያ የክትባቶች ተደራሽነትን ለማሻሻል የኮቪድ ክትባት የፈጠራ ባለቤትነት መብቶችን ለመተው ንግግር እያደረገች መሆኑን ተገለፀ፡፡
ብሪታኒያ ይህን የምታደርገው የኮሮና ክትባቶችን ማጋበስ እንዲቆም እና የክትባቶቹ የፈጠራ ባለቤትነት መብቶች እንዲቀሩ የሚጠይቁ ጫናዎች መበርታታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወረርሽኝ ብዙዎችን በቀጠፈበት በ1980 ዎቹ እና በ ‘90 ዎቹ ተመሳሳይ ነገር አጋጥሞ እንደነበር ለዚ-ጋርዲያን የተናገሩት የአይድስ ሄልዝኬር ፋውንዴሽን መስራቹ ሚካኤል ዊንስቴይን ጉዳዩን በፍጥነት መፍትሄ ካልተበጀለት ኮቪድን በዓለማችን ድሃ ሀገራት እንዲዛመት ፈቀድን እንደማለት ነው ብለዋል፤ ይህ መሆኑ ከፍተኛ “የሞራል እና የህብረተሰብ ጤና ድቀት” ሊያስከትል እንደሚችል በመጠቆም፡፡
ድሃ ሃገራት በተለይም የአፍሪካ ሃገራት ሃብታም ሃገራት ያገኙትን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድሃኒትን ለማግኘት እ.ኤ.አ ከ1996 እስከ 2003 መጠበቅ ግድ ብሏቸው እንደበርም አስታውሰዋል፡፡
ድርጅታቸው ብሪታኒያ እና የአውሮፓ ህብረት በዓለም ዙሪያ የክትባት ፍትሀዊ ተደራሽነት እንዲያሻሻሉ ያለመና “ቫክሲኔት አወር ወርልድ” የተሰኘ ዘመቻ ሰሞኑን መጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ብሪታኒያ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሃገራት ይሆናል በሚል በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ለተዘጋጁ የአስትራ ዜኔካ ክትባቶች የገንዘብ ድጋፍ አድርጋለች፡፡
ክትባቱ ሴረም በተሰኘው የህንድ መድሃኒቶች አምራች ኩባንያ ተመርቶ በዝቅተኛ ዋጋ የሚቀርብ ሲሆን በኮቫክስ ግዢ ስርዓት ለታቀፉ ሃገራት ከሚቀርቡ ክትባቶች የ98 በመቶ ያህሉን ድርሻ ይይዛል፡፡
ሆኖም አቅርቦቱ በተባለለት ልክ አይደለም፡፡ በኮቫክስ የተገዙ 140 ሚሊዬን ክትባቶችም ገና አልቀረቡም፡፡
በህንድ ያለው የቫይረሱ ስርጭት መክፋቱን ተከትሎም የክትባቶቹ ስርጭት ቆሟል፡፡ ይህ በተለይም በአፍሪካ ከፍተኛ የክትባት እጥረትን ፈጥሯል፡፡
ለዚህም ነው “የፈጠራ ባለቤትነት መብቶቹ ቀርተው ክትባቱን እኛም እናምርት” የሚለው ምክረ ሃሳብ ለዓለም የንግድ ድርጅት የቀረበው፡፡ ምክረ ሃሳቡ በደቡብ አፍሪካና ህንድ የቀረበ ነው፡፡
አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች 100 ሃገራትም ደግፈውታል፤ ሆኖም ገና በዓለም የንግድ ድርጅት አልጸደቀም፡፡
ጫናው የበረታባቸው ብሪታኒያ እና ሌሎች ክትባቶችን ያጋበሱ የአውሮፓ ሃገራት ግን ልክ እንደነ አሜሪካ ሁሉ የፈጠራ ባለቤትነት መብቶችን በመተው ፍትሐዊ የክትባት ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ በማሰብ ላይ መሆናቸው ተነግሯል፡፡