የእስራኤል ጦር አንድም የሊባኖስን መንደር መቆጣጠር እንዳልቻለ ሂዝቦላህ ተናገረ
ሂዝቦላህ እና የእስራኤል ጦር የፊት ለፊት የምድር ውጊያ ከጀመሩ 45 ቀን ሆኗቸዋል
እስራኤል በበኩሏ ሂዝቦላህን ከድንበራችን አባረናል የተኩስ አቁም ሊደረግ ይችላል ብላለች
የእስራኤል ጦር አንድም የሊባኖስን መንደር መቆጣጠር እንዳልቻለ ሂዝቦላህ ተናገረ፡፡
ከ13 ወራት በፊት የፍልስጤሙ ሐማስ በእስራኤል ላይ ያልታሰበ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ ነበር በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት የተጀመረው፡፡
ከሐማስ ጎን መሆኑን የገለጸው የሊባኖሱ ሂዝቦላህ በእስራኤል ላይ የአየር ጥቃቶችን ሲደርስ የቆየ ሲሆን ከ45 ቀናት በፊት እስራኤል ጦሯን ወደ ሊባኖስ አስገብታለች፡፡
ባለፉት ቀናት እስራኤል የሂዝቦላህ ዋና ሃላፊን ጨምሮ በርካታ ወታደራዊ አመራረሮችን በቤሩት እና ሌሎች ከተሞች ገድላለች፡፡
ሂዝቦላህ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ጦር በ45 ቀናት በቆየው ጦርነት ውስጥ እንድ መንደር እንኳን መቆጣጠር አልቻለም ብሏል፡፡
የሂዝቦላህ ቃል አቀባይ የሆኑት ሞሀመድ አፊፍ በደቡባዊ ሊባኖስ በሰጡት መግለጫ እስራኤል ጦሯን ወደ ሊባኖስ ብትልክም እስካሁን የያዘችው ቦታ የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በእስራኤል-ሄዝቦላህ ጦርነት ምን አዳዲስ ክስተቶች አሉ? እስካሁን የምናውቀው…
እስራኤል በበኩሏ ከሂዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ስለሚደረግበት ሁኔታ ፍንጭ ሰጥታለች፡፡
የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጊዲዮን ሳር እንዳሉት ሂዝቦላህን ከእስራኤል ድንበር አባረናል፣ ከእንግዲህ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መታጠቅ አይችልም፣የተኩስ አቁም ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ሂዝቦላህ በሶሪያ በኩል ጥቃት እንዳይከፍት ሩሲያ ልታስቆም እንደምትችልም ተናግረዋል፡፡
ይሁንና በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉ ሌሎች ሀይሎችን በሚመለከት የተኩስ አቁም ለማድረግ የተጀመረ ነገር እንደሌለም ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡