የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባለፈውን ሳምንት ተመን ያስቀጠለ ሲሆን 1 ዶላር በ112 ብር እየገዛ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የባለፈውን ሳምንት ተመን አስቀጥሏል።
በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ112.3957 ብር እየገዛ በ123.6353 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ዳሽን ባንክ በመደበኛው የውጭ ምንዛሬ ተመኑ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112.9888 ብር እየገዛ በ127.1124 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ኦሮሚያ ባንክ የውጭ ሀገራት ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ተመን ይፋ ሲያደርግ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112.6310 ብር እየገዛ በ127.6529 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው የጠቆመው።
አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ ዛሬ ጥቅምት 2 2017 አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ112.5000 ብር እየገዛ በ126 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ንብ ባንክም መደበኛውን (እለታዊ የምንዛሬ ተመን) ይፋ አድርጓል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላር በ113.0428 ብር እየገዛ በ126.6079 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።