ሄዝቦላህ ከእስራኤል የተቃጣበትን ጥቃት ለመመከት አዲስ ወታደራዊ እዝ ፈጠረ
ምንጮች “አዲስ የተቋቋመው የሄዝቦላህ እዝ አሁን የማጥቃት ጦርነት እያካሄደ ነው” ብለዋል
ሄዝቦላህ ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያላዋለቻው አደገኛ ሚሳዔሎችን ጨምሮ በርካታ ጦር መሳሪያዎችን አሁንም ታጥቋል
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ ከፍተኛ መሪዎቹ በእስራኤል መገደለቸውን ተከትሎ በደቡባዊ ሊባኖስ ለረጅም ጊዜ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን ምንጮች አረጋግጠዋል።
በኢራን የሚደገፈው ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ለሚኖረው የተራዘመ ጦርነትም አዲስ ወታራዊ እዝ መመስረቱን ነው ሮይተረስ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ የዘገበው።
አዲሱ የሄዝቦላህ ወታራዊ እዝ ሮኬቶች እንዲቶከሱ ትእዛዝ የሚሰጥ እና ከእስራኤል ጋር የእግረኛ ውጊያን የሚያከናውን መሆኑም ለድርጅቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ያረጋገጡት።
ሄዝቦላህ አሁንም ቢሆን በርካታ መሳሪያዎች በእጁ እንዳለ የሚነገር ሲሆን፤ ከታጠቃቸው መሳሪያዎች መካልም ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ ያላዋላቸው አደገኛ ሚሳዔሎች ይገኙበታል ነው የተባለው።
የሄዝቦላህ መሪ ሀሰን ነስረላህ በእስራኤል መገደሉን ተከትሎ ቡድኑ ጦር ለተወሰኑ ቀናት ተስተጓጉሎ ነበር የተባለ ሲሆን፤ መሪው ከተገደለ ከ72 ሰዓታት በኋላ አዲስ የኦፕሬሽን ክፍል ተቋቁሞ ወደ ውጊያ እንደገባ መደረጉን ነው ምንጮቹ ተናገሩት።
አዲሱ የዕዝ የእስራኤል ጥቃት ቢደርስበትም ስራውን እንደቀጠለ ሲሆን፤ በተለይም በደቡብ ሊባኖስ የሚገኙ ተዋጊዎች ከእዙ በሚደርሳቸው ትእዛዝ መሰረት ሮኬቶችን በመተኮስ እና መዋጋት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።
ለሄዝቦላህ ቅርብ የሆነ ከፍተኛ ባለስልጣን አዲስ የተቋቋመው እዝ አሁን የማጥቃት ጦርነት እያካሄደ ነው ብሏል።
ስማቸው ያልተገለጸ የሄዝቦላህ የጦር አዛዥ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት አዲሱ እዝ በጠቅላላ በሚስጥር እንደሚሰራ በመግለጽ፤ ስለ አወቃቀሩ ምንም ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጠም።
መሪው ከሁለት ሳምንት በፊት በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደለበት ሄዝቦላህ እስካሁን አዲስ መሪ ያልመረጠ ሲሆን፤ ተተኪ መሪ ይሆናሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ሰዉም በእስራኤል መገደላቸው ይታወሳል።
በሄዝቦላህ ላይ በአየር ድብደባ ጥቃት መሰንዘር የጀመረችው እስራኤል ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ እግረኛ ጦሯን ወደ ሊባኖስ በመላክ ውጊያ ጀምራች።
የሊበኖሱ ቡድን ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር በገጠመው ጦርነት በእስራኤል ጦር ላይ የተሳኩ ጥቃቶችን መሰንዘሩን ያስታወቀ ሲሆን፤ የእስራኤል ወታደሮችን እንደገደለም አስታውቋል።