ጀርመን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን ድጋሚ እንድታስጀምር ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠየቁ
ዩክሬን ከተሸነፈች ሩሲያ ቀጥተኛ የጀርመን ስጋት ትሆናለች ያሉት ፓርቲዎቹ ወታደራዊ አቅሟን በጦር መሳርያ እና የሰው ሀይል እንድታጠናክር ጠይቀዋል
ያለፈው የፈረንጆቹ አመት የአውሮፓ አህጉር ከቀዝቀዛው ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ያወጣበት ነበር
በ2011 ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን የሰረዘው የጀርመን ፓርቲ አሁን ላይ ድጋሚ ወደ ስራ እንዲገባ እየቀሰቀሰ ይገኛል፡፡
የክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን (ሲኤስዩ) ፓርቲ መሪ ማረከስ ሶደር ጀርመን ድሮኖችን ጨምሮ የተለያዩ የጦር መሳርያ ግዢዎችን ለመፈጸም እንዲሁም የብሔራዊ ውትድርናን ድጋሚ ወደ ስራ ለመመለስ አዋጅ ማውጣት አለባት ብለዋል፡፡
የጀርመን እራሷን የመከላከል አቅም በመጪው ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ ይችላል ያሉት የፓርቲው መሪ ይህ ከመሆኑ በፊት መንግስት አካባቢያዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በማየት አዳዲስ ወታደራዊ አቅም ማሳደጊያ ስትራቴጂዎችን ሊነድፍ ይገባል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ጨምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት ለጦር መሳርያ ግዢ እና ለወታደራዊ ወጪዎች የሚመድቡት ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ሲኤስዩ ፓርቲም በምስራቅ አውሮፓ በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ዩክሬን የምትሸነፍ ከሆነ ጀርመን ቀዳሚዋ የሞስኮ ስጋት የሚጋረጥባት ሀገር ልትሆን እንደምትችል ነው ያሳሰበው፡፡
በጀርመን ተግባራዊነት ላይ የነበረው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት አሁን ላይ የሀገሪቱ ወታደራዊ አቅም እንዲጠናከር በሚጠይቀው ሲኤስዩ ፓርቲ በ2011 ነበር ከስራ ውጭ እንዲሆን የተደረገው፡፡
ስለዚህ ጉዳይ የተጠየቁት የፓርቲው መሪ ማርከስ ሶደር “በ13 አመታት ውስጥ በርካታ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል። የብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ በምንም አይነት ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ የሚከት አጋጣሚ ሲፈጠር ሀገራት ከጊዜው ጋር አካሄዳቸውን መለወጥ ይጠበቅባቸዋል” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በአውሮፓ ከሚገኙ ሀገራት የጀርመን ብሔራዊ ጦር ዝቅተኛ በጀት ያለው እንደሆነ የተናገሩት የፓርቲ መሪው “የኦላፍ ሾልዝ አስተዳደር ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በቅጡ ስለመገንዘቡ በእርግጠኝነት ለማናገር እቸገራለሁ” ብለዋል፡፡
የአሁኑ የጀርመን የመከላከያ ሚንስትር ጦሩን ለማጠናከር የተለያዩ አዳዲስ ሀሳቦች ቢኖራቸውም በገዛ መንግስታቸው በቂ ድጋፍ እያገኙ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
በዚህ አመት መጀመርያ የመከላከያ ሚንስትሩ ሁለት የተለያዩ ጦሩን በሰው ሀይል የማጠናከርያ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡
የመጀመርያው በዘመቻ መልክ በበጎ ፈቃድ ጦሩን የሚቀላቀሉ ጀርመናውያንን መመዝገብ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ብሔራዊ ውትድርናን ከ18 አመት ጀምሮ በማስጀመር የሀገሪቱን ቋሚ እና ተጠባባቂ ጦር ማጠናከርን አላማው አድርጓል፡፡
በዚህም በበጎ ፈቃደኛ ብቻ 40 ሺህ የሚጠጉ ጀርመናውያንን ለመመልመል ለመንግስት ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
በ2023 የአውሮፓ አህጉር ወታደራዊ በጀት 552 ቢሊየን ፓውንድ ደርሷ፤ ይህም ከቀዝቀዛው ጦርነት በኋላ ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ የተደረገበት አመት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡