የባህረ ሰላጤው ሀገራት እስራኤል ኢራንን ለማጥቃት የአየር ክልላቸውን እንዳትጠቀም ከለከሉ
እስራኤል በኢራን የነዳጅ ማውጫዎች ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም አሜሪካ ጫና እንድታደርግም ጠይቀዋል
ሀገራቱ ግጭቱ ከተባባሰ በቀጠናው ከሚገኙ ኢራን የምትደግፋቸው ታጣቂዎች በነዳጅ ማውጫ ቦታዎች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ስጋት ላይ ናቸው
የባህረ ሰላጤው ሀገራት እስራኤል ኢራንን ለማጥቃት የአየር ክልላቸውን እንዳትጠቀም ከለከሉ።
የባህረ ሰላጤው ሀገራት እስራኤል በኢራን ላይ ለምትፈጽመው የአጸፋ ጥቃት የአየር ክልልቸውን እንዳማይፈቅዱ አስታወቁ፡፡
ሀገራቱ የእስራኤል ሚሳይሎች እና የጦር ጄቶች አየር ክልላቸውን አቋርጠው ማለፍ እንደማይችሉ ነው የገለጹት፡፡
ከሰሞኑ ሳኡዲ አረቢያ እና ኳታርን ጨምሮ በሌሎች የባህረሰላጤው ሀገራት ጉብኝት ያደረጉት የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አባስ አራግቺ፤ እስራኤል ትፈጽመዋለች ተብሎ ለሚጠበቀው የአጸፋ ምላሽ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት የአየር ክልላቸውን እንዳይፈቅዱ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ሚንስትሩ ቢዚህ ወቅት የትኛውንም የባህረ ሰላጤው ሀገር የአየር ክልልም ሆነ ወታደራዊ ካምፕ መነሻ አድርጎ በኢራን ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ቴሄራን ከሁሉም የባህረ ሰላጤው ሀገራት የተቃጣ ጥቃት አድርጋ እንደምትወስደው አስጠንቅቀዋል፡፡
ሳኡዲ አረብያ ፣ኳታር እና አረብ ኢምሬትስ የአየር ክልላቸውን ለእስራኤል ጥቃት መዋያነት እንዳያገለግል ዝግ ካደረጉ የአካባቢው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
የቴሄራን ባለስልጣናት ሳኡዲ አረብያን ጨምሮ ሌሎች የአካባቢው ሀገራት የአየር ክልላቸውን ለቴልአቪቭ ጥቃት ክፍት የሚያደርጉ ከሆነ በአካባቢው የሚገኙ የኢራን አጋሮች በነዳጅ ማውጫ ጣብያዎች ላይ ጥቃት ሊፈጽሙ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸውን ሮይተርስ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
ከዚህ ባለፈም የባህረ ሰላጤው ሀገራት በአሜሪካ ላይ ያላቸውን ተጽእኖ በመጠቀም እስራኤል በኢራን ላይ የነዳጅ ማውጫ ጣብያዎች ላይ ጥቃት እንዳትፈጽም ዋሽንግተን ጫና እንድታደረግ በማግባባት ላይ እንደሚገኙ ነው የተነገረው፡፡
የባህረ ሰላጤው ባለስልጣናት ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር በመገናኘት እስራኤል ልትወስደው የምትችለው የበቀል እርምጃ በቀጠናው ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመከላከል ጥረት እንዲደረግ መመካከር ጀምረዋል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ የሚመራው የነዳጅ ላኪ ሀገራት ድርጅት ኦፔክ የእስራኤል የበቀል እርምጃ በኢራን የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ የሚፈጸም ከሆነ በዚህ ሊፈጠር የሚችል የአቅርቦት እጥረትን ለማካካስ የሚያስችል በቂ የነዳጅ ክምችት እንዳለው አስታውቋል፡፡
ነገር ግን ከእስራኤል ጥቃት ጋር በተያያዘ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ የነዳጅ አምራች በሚባሉት አረብ ኢምሬትስ እና ሳኡዲ አረቢያ የነዳጅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ ጉዳት ቢደርስ አለም ከፍተኛ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ሊገጥማት ይችላል ተብሏል፡፡