በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን የዶላር ዋጋ ስንት ደረሰ?
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዶላር መግዣ ዋጋውን የትናንቱን ሲያስቀጥል በመሸጫው ላይ ቅናሽ አድርጓል
ልማት ባንክ አንድ ዶላር በ116 ብር ገዝቶ በ123.72 ብር እየሸጠ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
የ2017 አዲስ ዓመት አስመልክቶም ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ የሚያበረርታታ ተመን እያወጡ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ በዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል የሚላክን ገንዘብ ከባንኩ ለሚቀበሉ ደንበኞቹ ተጨማሪ የ6.82 በመቶ የበዓል ስጦታ እንደሚሰጥ አስታውቋል።
ባንኩ ዛሬ መስከረም 9 2017 ዓ.ም መደበኛ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የመግዣ ዋጋውን የትናንቱን አስቀጥሎ በመሸጫው ላይ ቅናሽ አድርጓል። በዚህም አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ112.3957 ብር እየገዛ በ123.6353 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ዳሸን ባንክ በዓልን ምክንያት በማድረግ ልዩ የምንዛሬ ዋጋ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም በሃዋላ የሚላክ 1 ዶላርን ከመደበኛው የምንዛሬ ዋጋ ላይ እስከ 16 በመቶ ጉርሻ እንደሚሰጥ ማሳወቁ ይታወቃል።
ባንኩ በመደበኛ የምንዛሬ ዋጋው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ112.3989 ብር እየገዛ በ126.4488 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ ያደረገው።
እስከ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባለው ጊዜ የሚላክን አንድ የአሜሪካ ዶላር በ125 ብር እንደሚመነዝር ያስታወቀው ንብ ባንክም መደበኛውን (እለታዊ የምንዛሬ ተመን) ይፋ አድርጓል።
በዚህም ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ108.0994 ብር እየገዛ በ121.0714 ብር እየተሸጠ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሰሞኑን የውጭ ምንዛሬ ተመን ያስቀጠለ ሲሆን አንድ ዶላርን በ116.0100 ብር ገዝቶ በ123.7200 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።