ዩክሬን በሩሲያ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ
ሩሲያ እና ዩክሬን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ በደርዘን በሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቃት ማድረሳቸውን እየገጹ ይገኛሉ
ዩክሬን ሩሲያን ከግዛቷ ለማስወጣት፣ ሩሲያ ደግሞ በምስራቅ ዩክሬን ያሉ አራት ግዛት ሙሉ በሙሉ ለመያዝ በማለም እያደረጉት ያለው ጦርነት ቀጥሎ 31 ወራትን አስቅጥሯል
ዩክሬን በሩሲያ በፈጸመችው የድሮን ጥቃት ከባድ ፍንዳታ ተከሰተ።
ዩክሬን በዛሬው እለት በትቨር ግዛት በሚገኝ የሩሲያ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ላይ በፈጸመችው መጠነሰፊ የድሮን ጥቃት ከባድ ፍንዳታ መከሰቱ በቅርብ የምትገኘው ከተማ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ማድረጉን ሮይተርስ የአይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በማህበራዊ ሚዲያ የተለቀቀው ያልተረጋገጠ ቪዲዮ እና ምስሎች ከሞስኮ በስተምዕራብ በኩል 380 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው ሀይቅ ላይ ጭስ ወደ ሰማይ ሲወጣ እና በርካታ ፍንዳታዎችን ሲፈነዱ አሳይተዋል።
"ጠላት በቶሮፔት የሚገኘውን የመሳሪያ ማከመቻ መትቷል" ሲል የሩሲያ ደጋፊ ወታደራዊ ጸኃፊ ዩሪ ፖዶሊያካ ተናግረዋል። "በእዚያ ያለ መፈንዳት የሚችል ሁሉ ፈንድቷል።"
የሩሲያ ሚዲያዎች ከዚህ በፊት ለግንባር የሚሆኑ የጦር መሳሪያ ማከማቻ በዚህ ቦታ እንደሚገኝ መዘገባቸውን ዘገባው ጠቅሷል።
የትቨር ግዛት አስተዳዳሪ ኢጎር ሩደንያ የዩክሬን ድሮን ተመትቶ መውደቁን እና በዚህ ምክንያት እሳት መነሳቱን እና ነዋሪዎች ከቦታው እንዲወጡ መደረጉን ገልጿል። አስተዳዳሪው እየነደደ ያለው ምን እንደሆነ አልጠቀሰም።
ሮይተርስ የዩክሬን የደህንነት ምንጭ ጠቅሶ እንደዘገበው የድሮን ጥቃቱ ሚሳይሎችን፣ ጋይድ ቦምቦችን እና የከባድ መሳሪያ ተተኳሾችን ማከማቻ መጋዘንን አውድሟል።
ሩሲያ እና ዩክሬን አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ በደርዘን በሚቆጠሩ ድሮኖች ጥቃት ማድረሳቸውን እየገጹ ሲሆን ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ወደፊት እየገፋች ነው።
ዩክሬን ሩሲያን ከግዛቷ ለማስወጣት፣ ሩሲያ ደግሞ በምስራቅ ዩክሬን ያሉ አራት ግዛት ሙሉ በሙሉ ለመያዝ በማለም እያደረጉት ያለው ጦርነት ቀጥሎ 31 ወራትን አስቅጥሯል።
ዩክሬን በምስራቅ ዩክሬን ያለውን የሩሲያ ኃይል አሰላለፍ ለማዛባት፣ በምዕራብ ሩሲያ ኩርስክ ግዛት ድንገተኛ ጥቃት በመክፈት በርካታ ቦታዎችን መያዝ ችላ ነበር። ነገርገን ሩሲያ በዚህ ዩክሬን ጥቃት ጦሯን ወደኋላ እንዲያፈገፍግ አላደረገችም።
ሩሲያ በተቃራኒው በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን እና በግንባር ላለው የዩክሬን ጦር ሎጂስቲክስ ለማመላለስ ወሳኝ የሆነችውን የፖክሮቭስክ ከተማን ለመያዝ ተቃረበች።
ዩክሬን ትርፍ አገኝበታለሁ ያለችው የኩርስክ ግዛት ጥቃት እንዳሰበችው ሳይሆንላት ቀረ። አሁን ላይ ሩሲያ በወሰደችው መልሶ ማጥቃት 10 የኩርስክ መንደሮችን ከዩክሬን ነጥቃለች።
ዩክሬን ምዕራባውያን ሀገራት የለገሷትን የረጅም ርቀት ሚሳይሎች በሩሲያ ምድር ላይ እንድትጠቀም እንዲፈቅዱላት እያግባባች ነው።
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ይህን የዩክሬን ጥያቄ እያጤኑት እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል። ሩሲያ ምዕራባውያን ፍቃድ እንዳይሰጡ አስጠንቅቃለች።