የባንኮች የአዲስ አመት የውጭ ምንዛሬ ተመን ምን ይመስላል?
የግል ባንኮች ከውጭ ሀገር በሃዋላ የሚላክ አንድ ዶላርን እስከ 125 ብር ድረስ እየመነዘሩ ነው
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አንድ ዶላር በ116 ብር እየገዛ በ122 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል
10ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች አዲሱን የምንዛሬ ተመን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
አዲስ አመት መቃረቡን ተከትሎ ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ እየጠየቁ ነው።
ዲያስፖራው በህገወጡ (ጥቁር ገበያ) ከመላክ ይልቅ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥ የሚያበረታታ ተመንም እያወጡ ሲሆን፤ ባንኮች በማህራዊ ትስስር ገጻቸው ባጋሩት የጳጉሜ 5 2016 የውጭ ምንዛሬ ተመን ዝርዝር ላይ የዋጋ ልዩነት ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የትናንቱን የምንዛሬ ዋጋ አስቀጥሎ አንድ ዶላርን በ108.0728 ብር እየገዛ በ119.9068 ብር እየሸጠ ይገኛል።
የእንግሊዝ ፓውንድ በ135.5141 ብር እየገዛ በ151.1231 ብር እንደሚሸጥም አስታውቋል።
ንብ ባንክ ከውጭ ሀገር በሐዋላ የሚላክ ዶላርን እስከ መስከረም 30 2017 በ125 ብር እንደሚመነዝር ይፋ አድርጓል።
ኦሮሚያ ባንክ ባንክ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ107.7687 ብር እየገዛ በ123.9340 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን የጠቆመው።
ወጋገን ባንክ እስከ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ ባንኩ አንድ ዶላር በ116 ብር ከተጨማሪ ጉርሻ ጋር እየገዛ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ደግሞ ከትናንቱ የሶስት ብር ጭማሪ አድርጎ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ116.0100 ብር እየገዛ በ122.7800 ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አድርጓል።