የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በሴናር ከተማ 31 ሰዎች መግደሉን የመብት ተሟጋች ቡድን ገለጸ
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ወደ ደቡብ ምስራቅ የሚያደርገው ግስጋሴ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ፍጥነቱን ቀንሷል
የተመድ ልኡክ አለምአቀፍ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ሱዳን እንዲገቡም ባለፈው አርብ ሀሳብ አቅርቧል
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በሴናር ከተማ 31 ሰዎች መግደሉን የመብት ተሟጋች ቡድን ገለጸ።
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር በደቡብ ምስራቅ ሱዳን በምትገኘው ሴናር ከተማ ላይ እንደአዲስ ጥቃት ከከፈተበት ከትናንት ጀምሮ ቢያንስ 31 ሰዎችን መግደሉን እና ሌሎች 100 የሚሆኑትን ደግሞ ማቁሰሉን የመብት ተሟጋች ቡድን ገልጿል።
የንጹሃን ሞትን እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን የሚከታተሉት የአደጋ ጊዜ የህግ ባለሙያዎች እንዳሉት ዋናውን የገበያ ቦታ ጨምሮ በርካታ የከተማዋ አካባቢዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ከባድ መሳሪያ ጥቃት ደርሶባቸዋል።
የሴናር ከተማ አብዛኛውን ክፍል እና ቢያንስ የሱዳንን ግማሽ የተቆጣጠረው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ወደ ደቡብ ምስራቅ የሚያደርገው ግስጋሴ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ፍጥነቱን ቀንሷል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ከሱዳን ጦር ጋር እያካሄደ ያለው ጦርነት በአለም ላይ ከባድ የተባለው የሰብአዊ ቀውስ እንዲፈጠር፣ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃኝ ሰዎች እንዲሞቱ እና አብዛኛው የሱዳን መሰረተልማት እንዲወድም አድርጓል።
የአደጋ ጊዜ የህግ ባለሙያዎቹ እንደገለጹት ከሆነ የሱዳን ጦር በሴናር ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በፈጸመው የአየር ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ተገድለዋል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ጦር ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ኢላማ ባደረጋት ኢል-ኦቤይድ በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት አንድ ሰው የተገደለ ሲሆን 17 ሰዎች ደግሞ ቆስተዋል።
የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች 18 ወራትን ባስቆጠረው የእርስበእርስ ጦርነት ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል ወንጀሎች ፈጽመዋል ያለው የተመድ ልኡክ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ሱዳን እንዲገቡም ባለፈው አርብ ሀሳብ አቅርቧል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ እለት በሰጠው ምላሽ የሰላም አስከባሪ ኃይል ወደ ሱዳን ይግባ የሚለውን የተመድ ሀሳብ ወድቅ አድርጎ፣ አለምአቀፍ ሰላም አስከባሪ ሀሳብ "የሱዳን ጠላቶች ምኞት ነው" ብሏል።