በባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተመን የዶላር ዋጋ ስንት ደረሰ?
የግል ንግድ ባንኮች አንድ ዶላርን እስከ 122 ብር እየገዙ እስከ 125 ብር በመሸጥ ላይ ናቸው
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ18 ቀናት በፊት ያወጣውን የምንዛሬ ተመን አስቀጥሏል
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ህዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ከ18 ቀናት በፊት ያወጣውን ተመን አስቀጥሏል። ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ119.2044 ብር እየገዛ፤ በ121.5885 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ዳሽን ባንክ ከሁለት ቀናት በፊት ያወጣውን የምንዛሬ ተመን ቢያስቀጥልም ከፍተኛውን የዶላር መግዣ ዋጋ ያቀረበ ባንክ ሆኗል። ባንኩ አንድ ዶላርን በ122.8506 ብር እየገዛ በ125.3076 ብር እየሸጠ መሆኑን ገልጿል።
ኦሮሚያ ባንክ እለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ላይ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ማሻሻያ አላደረገም። ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.3066 ብር እየገዛ በ123.7327 ብር እየሸጠ ይገኛል።
ብርሃን ባንክ ደግሞ ከአራት ቀናት በፊት ያወጣውን የምንዛሬ ተመን አስቀጥሎ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.5630 ብር እየገዛ በ123.9943 ብር እየሸጠ ነው።
ጸደይ ባንክ የህዳር 7 ቀን 2017 የውጭ ምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ በሳንቲሞች ጭማሪ አድርጎ ለአንድ የአሜሪካ ዶላር 120.9737 ብር መግዣ ዋጋ አቅርቧል።