ክትባቶችን በመቃወም የሚታወቁት ኬነዲ ጁኒየር የአሜሪካ ጤናን እንዲመሩ ተሾሙ
ዶናልድ ትራምፕ ሹመቱን በተቀነባበረ እና ጤና ባልሆኑ ምግቦች የተጎዱ አሜሪካዊያንን ጤና ለመመለስ በሚል እንደሰጡ ተናግረዋል
የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የኬነዲ ጁኒየርን ሹመት እየተቃወሙ ናቸው
ክትባቶችን በመቃወም የሚታወቁት ኬነዲ ጁኒየር የአሜሪካ ጤናን እንዲመሩ ተሾሙ፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተደርገው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ መንግስታቸውን ለማቋቋም በሂደት ላይ ሲሆኑ የሚሾሟቸውን ሰዎች እያዘጋጁ ናቸው፡፡
በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ላይ የግል እጩ ሆነው ሲወዳደሩ የነበሩት ሮበርት ኬነዲ ጁኒየር በዶናልድ ትራምፕ አስተዳድር ውስጥ የጤና ሚኒስትር ተደርገው እንደሚሾሙ ተገልጿል፡፡
ኬነዲ ጁኒየር በተለይም ክትባቶችን በመቃወም የሚታወቁ ሲሆን በዓለም ላይ ፍጹም ክትባት የለም በሚል አቋማቸውም ይታወቃሉ፡፡
ሰዎችን ክትባት አትውሰዱ አላልኩም የሚሉት ኬነዲ ጁኒየር እሳቸው ግን የትኛውንም ክትባት አልወስድም ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ለኬነዲ ጁኒየር ሹመቱን ባሳወቁበት የማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት በተቀነባበሩ እና ጤናማ ምግቦች የተጎዱ አሜሪካዊያንን ጤና ለመመለስ ሮበርት ኬነዲ ጁኒየርን ሾሜያለሁ ብለዋል፡፡
ኬነዲ ጁኒየር የአሜሪካ ጤና ስርዓትን እንደሚመሩ የሚጠበቅ ሲሆን በተለይም የጤና ፖሊሲዎችን፣ የክትባት ምርምር ስራዎችን፣ የመድሃኒት እና ምግብ ስርዓቶችን እንደሚመሩ ጠበቃል፡፡
የኬነዲ ጁኒየርን ሹመት ተከትሎ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ሲሆኑ የተወሰኑት ሹመቱን ተቃውመዋል፡፡
የአካባቢ ጤና ባለሙያ የሆኑት ኬነዲ ጁኒየር ከጤና ህጎች ጋር የተያያዙ ስራዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
የሮበርት ኬነዲ ሹመት ጥር ላይ ስራ በሚጀምረው አዲሱ የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል፡፡