የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ዶላርን በ119 ብር ገዝቶ በ121 ብር እየሸጠ ነው
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን ስርአት ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኗን ተከትሎ ባንኮች በየእለቱ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ መሃል ያለው ልዩነት እንዲቀራረብ ባሳሰበ ማግስት የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ ለውጥ ታይቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ ጥቅምት 30 2017 ዓ.ም የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ የሰሞኑን ዋጋ አስቀጥሏል። አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ119.2044 ብር እየገዛ ሲሆን፤ በ121.5885 ብር እየሸጠ መሆኑን አስታውቋል።
ጎህ ቤቶች ባንክ አንድ ዶላር በ121.5204 ብር ገዝቶ በ123.9508 ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ጠቁሟል።
ኦሮሚያ ባንክ እለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ላይ ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ማሻሻያ አላደረገም። ባንኩ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ121.3066 ብር እየገዛ በ123.7327 ብር እየሸጠ ይገኛል።
አቢሲኒያ ባንክ በዶላር መግዣው ላይ የሳንቲሞች ጭማሪ አድርጎ አንድ ዶላርን በ120.5001 ብር እየገዛ በ122.9101 ብር እየሸጠ መሆኑን በእለታዊ የምንዛሬ ተመኑ ይፋ አድርጓል።
ዳሽን ባንክ የጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም እለታዊ የምንዛሬ ተመኑን ይፋ ሲያደርግ የሰሞኑን ዋጋ አስቀጥሏል። በዚህም አንድ ዶላርን በ120.4570 ብር እየገዛ በ122.8661 ብር እየሸጠ መሆኑን ገልጿል።