ኔታንያሁ ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ
ጠቅላይ ሚንስትሩ የተኩስ አቁሙ ሄዝቦላን ድጋሚ በትጥቅ ከመደራጀት አያግደውም ብለዋል
ምዕራባውን በሊባኖስ እየደረሰ ያለው መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት እንዲቆም እና ሁለቱ ወገኖች ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እየጠየቁ ነው
ኔታንያሁ ከሄዝቦላህ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርጉ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከሄዝቦላ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የቀረበውን ሀሳብ እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑየል ማክሮን ሄዝቦላን ድጋሚ በትጥቅ ከመደራጀት የማያግድ የተኩስ አቁም ስምምነትን እንደማይቀበሉ እንደነገሯቸው ገልጸዋል፡፡
ኔታንያሁ በሄዝቦላህ ላይ የከፈትነው ዘመቻ ለሀገራችን ስጋት አለመሆኑን ለማረጋገጥ እና በሰሜኑ የሀገሪቱ ድንበር የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ ነው ማለታቸውን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ለፕሬዝዳነቱ የተላከው መልዕክት አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በቅርቡ ማክሮን በሊባኖስ እና እስራኤል ጉዳይ ደቡብ አፍሪካ እና አልጄርያን ጨምሮ ከሌሎች ሀገራት ጋር ለማድረግ ያሰቡትን ውይይት አስተዳደሩ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡
እስራኤል ራስን የመከላከል መሰረታዊ መብቷን ለመንፈግ እየሰሩ ከሚገኙ በትግባርም የመኖር መብቷን ከሚቃወሙ ሀገራት ጋር የሚደረግ ውይይት እና ውሳኔን አትቀበልም ብለዋል ኔታንያሁ፡፡
ኢማኑኤል ማክሮን እስራኤል በሊባኖስ እያደረሰችው የምትገኝውን መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት ከሚቃወሙ የምዕራባውያን መሪዎች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንቱ በሄዝቦላ እና በኔታንያሁ መንግስት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ እንዲሁም ወደ ጋዛ እና ሊባኖስ የሚላኩ የጦር መሳርያ ድጋፎች እንዲቆሙ በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
ሰኞ እለት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝው ከ50 ሀገራት የተውጣጡ አባላትን የያዘውን የተመድ ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲወጣ ያቀረበችውን ጥያቄ ፈረንሳይ ተቃውማለች፡፡
ከፈረንሳይ ባለፈ አሜሪካ በሊባኖስ እየተፈጸመ የሚገኝው የጥቃት መጠን ላይ ቅሬታዋን እየገለጸች እንደምትገኝ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
የሄዝቦላህ ዋና መሪ ሃሰን ናስረላህ ከመገደላቸው ቀደም ብሎ በነበሩት ቀናት በ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በተመሳሳይ የሄዝቦላህ እና እስራኤል ግጭት ወደ መባባሱ ሳይገባ የ21 ቀናት የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተጠይቆ ይሁንታ ማጣቱ ይታወሳል፡፡
የሀማስ እና እስራኤል ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ሮኬት ማስወንጨፍ የጀመረው ሄዝቦላህ በጋዛ የሚደረገው ጦርነት እስካልቆመ ድረስ በእስራኤል ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እንደማያቆም ለድርድርም እንደማይቀመጥ አሳውቆ ነበር፡፡
በቅርቡ የሊባኖስ ፓርላማ አፈጉባኤ ከምዕራባውያን ሀገራት እና ከቀጠናው አጋሮች ጋር በመተባበር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እያደረጉት በሚገኘው ጥረት ከቡድኑ ይሁንታን ማግኝታቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡
ሄዝቦላህ እስከዛሬ ሲያቀርባቸው የነበሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ሙሉ ለሙሉ በመተው ከእስራኤል ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ነኝም ብሏል፡፡