ዛሬ ነሃሴ 30 በባንኮች 1 ዶላር በስንት ብር እየተገዛና እየተሸጠ ነው?
ባንኮች ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ምንዛሬ በህጋዊው መንገድ እንዲልኩ የሚያበረታታ ተመን እያወጡ ነው
ዲያስፖራው በዚህ አመት በሬሚታንስ ወደ ኢትዮጵያ የላከው ከ6 ቢሊየን ዶላር በላይ መድርሱ ተገልጿል
አዲስ አመት መቃረቡን ተከትሎ ባንኮች በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያውን በባንኮች አማካኝነት ገንዘብ እንዲልኩ እየጠየቁ ነው።
ዲያስፖራው በህገወጡ (ጥቁር ገበያ) ከመላክ ይልቅ ህጋዊውን መንገድ እንዲመርጥ የሚያበረታታ ተመንም እያወጡ ነው።
ወጋገን ባንክ በትናንትናው እለት እስከ መስከረም 30 2017 የሚቆይ ልዩ የውጭ ምንዛሬ ተመን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፥ ባንኩ አንድ ዶላር በ115 ብር ገዝቶ በ119 ብር እንደሚሸጥ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ባለፈው ሳምንት ከነበረው የውጭ ምንዛሬ ተመን የተሻሻለ ዋጋ አውጥቷል።
ባንኩ ዛሬ ነሃሴ 30 2016 የውጭ ሀገር ገንዘቦችን የሚገዛበትን እና የሚሸጥበትን ዋጋ ይፋ ሲያደርግ አንድ ዶላር በ106.3684 ብር ገዝቶ በ118.0689 ብር እየሸጠ መሆኑን ነው ያስታወቀው።
ዳሽን ባንክ ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ዋጋ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ106.3705 ብር እየገዛ በ119.6668 ብር እየሸጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
ኦሮሚያ ባንክ በበኩሉ አንድ ዶላር በ106.1742 ብር እየገዛ በ119.9768 ብር እየሸጠ መሆኑን ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ተመን ይፋ አድርጓል።
አቢሲኒያ ባንክ ደግሞ 1 ዶላር በ107.54950 ብር እየገዛ በ120.4554 ብር እየገዛ መሆኑን ነው የገለጸው።
ዳሽን ባንክ ባወጣው እለታዊ የምንዛሬ ዋጋ አንድ የአሜሪካ ዶላርን በ106.3705 ብር እየገዛ በ119.6668 ብር እየሸጠ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ስርአት ተግባራዊ ማድረጓ የባንኮች እና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚያጠብ ታምኖበታል።
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም በባንኮች ገንዘብ እንዲልኩ እንደሚያበረታታ የሚጠበቅ ሲሆን ባንኮች እያቀረቡት ያለው ተመንም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንዲገባ ያደርጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው በ2016 በጀት አመት ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ የላከው 6 ቢሊየን ዶላር ደርሷል።