የቀድሞው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በስልጣን ላይ እያሉ እስራኤል ከአረብ ሀገራት ጋር የተሻለ ሰላም እንዲኖራት የሚያደርግ ስምነት እንዲፈረም ምክንያት ሆነው ነበር ተብሏል
ዶናልድ ትራምፕ ለሰላም ኖቤል ሽልማት ታጩ፡፡
የዓለማችን ልዕለ ሀይል ሀገር የሆነችው አሜሪካንን ከ2016 እስከ 2020 ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዶናልድ ትራምፕ የዘንድሮው የሰላም ኖቤል ሽልማት እንዲወስዱ ታጭተዋል፡፡
በዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው እንደሚወዳደሩ የሚጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ለዚህ ሽልማት ሲታጩ ለአራተኛ ጊዜ እንደሆነ ፎክስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ለሽልማት የታጩት በስልጣን ላይ እያሉ የአብርሃም ስምምነት በሚል እስራኤል፣ ባህሬን እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በሪፐብሊካን ፓርቲው የምክር ቤት አባል ክላውዲያ ቴኒ የተጠቆሙት ዶናልድ ትራምፕ በመካከለኛው ምስራቅ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖር አድርገዋል በሚል እንደጠቆሟቸው ተናግረዋል፡፡
በመካከለኛው ምስራቅ አሁን ላይ ያለው ውጥረት እና የደህንነት ችግር የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ደካማ አስተዳድር ውጤት ነው ያሉት እኝህ የምክር ቤት አባል ትራምፕ በስልጣን ላይ ቢሆን ይህ ሊከሰት እንደማይችል ተናግረዋል፡፡
አውሮፓ ህብረት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሊመጡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳለው ተገለጸ
የ2024 የኖቤል ሽልማት እጩዎች በየሽልማት ዘርፉ ማስገባት የተጀመረ ሲሆን የፊታችን ጥቅምት ወር ላይ የሰላም ኖቤል ሽልማትን ጨምሮ በሌሎችም ዘርፎች አሸናፊዎች ይፋ ማድረግ ይጀመራል፡፡
የ2023 የሰላም ኖቤል ሽልማትን ኢራናዊቷ ናርገስ ሞሀመዲ ያሸነፈች ሲሆን ይህች የሰብዓዊ መብት ታጋይ አሁንም በኢራን እስር ላይ ትገኛለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በፈረንጆቹ 2019 ላይ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለዓመታት የቆየው ግጭታቸው እንዲያበቃ እና የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲዳብር አድርገዋል በሚል የሰላም ኖቤል ሽልማት ማሸነፋቸው ይታወሳል፡፡