የቀድሞው ፕሬዝዳንት በ200 ሺህ ዶላር ዋስ ከእስር መፈታታቸው ይታወሳል
ዶናልድ ትራምፕ ከታሰሩ በኋላ ገበያ ደርቶላቸዋል ተባለ።
አሜሪካንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ ባሉት አራት ዓመታት በፕሬዝዳንት የመሩት ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫ ጋር በተያያዘ 91 ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ በጆርጂያ ግዛት የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለማስቀየር በሚል የህግ ጥሰት ፈጽመዋል በሚል ለእስር ተዳርገዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት በእስር ቤት በአካል ቀርበው እጅ የሰጡ ሲሆን ከታሰሩ 20 ደቂቃ በኋላ 200 ሺህ ዶላር ከፍለው በዋስ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ሲታሰሩ የተነሱትን ፎቶ ደጋፊዎቻቸው በቲሸርት፣ ትኩስ ነገሮች መጠጫ ኩባያዎች እና ሌሎች አልባሳት ላይ እያተሙ ለገበያ እያቀረቧቸው ነው።
ከዶናልድ ትራምፕ የእስር ቤት ፎቶዎች ጋር "እጅ እንዳሰጥ"፣ "አሜሪካንን እንታደግ"፣ "ትራምፕ ነጻ ነው" የሚሉ መልዕክቶችን አብረው አትመውባቸዋል ተብሏል፡፡
ለዶናልድ ትራምፕ እና ፓርቲያቸው ሪፐብሊካን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ተብለው የተጀመሩት እነዚህ ህትመቶችን የሚሸምቱ ሰዎች ቁጥር እንደጨመረ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ምስል የያዙት እነዚህ ህትመቶች ከ15 እስከ 55 ዶላር በመሸጥ ላይ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
የሕትመቶቹ ፈላጊዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ያልሆኑ ግለሰቦች እና ተቋማት ሳይቀር ወደ ገበያው እየገቡ ስለመሆኑ ነው የተዘገበው።
በ2024 የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ እጩ የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ የተመሰረተባቸው ክሶች ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸው እንጂ እኔ አንዳቸውንም አልፈጸምኩም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የዓለማችን ቀዳሚ ባለጸጋ አሜሪካዊው ኢለን መስክ ከዚህ በፊት በዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ ከተመሰረተ ምርጫውን በሰፊ ድምጽ የማሸነፍ እድላቸው ሰፊ ይሆናል ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡