ዶናልድ ትራምፕ 83 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለቀድሞዋ ጋዜጠኛ ጂን ካሮል ካሳ እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት ተወስኖባቸዋል
ጂን ካሮል ዶናልድ ትራምፕ አስገድዶ ደፍረውኛል በሚል ክስ መስርተው ነበር
ዶናልድ ትራምፕ 83 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው።
የአሜሪካ 45ኛው ፕሬዝዳንት በመሆን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ ያገለገሉት ዶናልድ ትራምፕ በያዝነው ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር የምርጫ ቅስቀሳቸውን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በዶናልድ ትራምፕ ላይ ከዚህ በፊት የወሲብ ፊልም ተዋናይ ለሆነችው ስቶርም ዳንኤልስ ከተባለች እንስት ጋር የፈጸሙት ድርጊት ለህዝብ ይፋ እንዳይሆን በድብቅ ክፍያ ፈጽመው ግብር አጭበርብረዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡
አሁን ደግሞ በፋሽን ጉዳዮች ዙሪያ ጸሃፊ የሆኑት ጂን ካሮል የተሰኘች እንስት ከ28 ዓመት በፊት በዶናልድ ትራምፕ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው የመሰረቱት ክስ ውሳኔ አግኝቷል፡፡
የ79 ዓመቷ ጂን ካሮል በአስገድዶ መደፈር ወንጀሉ በተፈጸመባቸው ወቅት የነበረው ስሜት አሁን ድረስ እንደሚሰማቸው የተናገሩ ሲሆን በመልበሻ ክፍል ውስጥ የውስጥ ልብስ እየለኩ እያለ በትራምፕ መደፈራቸውን ተናግረዋል፡፡
በማንሀተን ፍርድ ቤት በተካሄደው ክርክር ዶናልድ ትራምፕ 83 ሚሊዮን ዶላር የስም ማጥፋት ካሳ እንዲከፍሉ ታዘዋል።
ዶናልድ ትራምፕ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው በሚል ውሳኔውን የተቃወሙ ሲሆን ይግባኝ እንደሚሉም ተናግረዋል።
ከሳሽ ጂን ካሮል በበኩሏ ትራምፕ አስገድዶ ከደፈረኝ በኋላ መካዱን ተከትሎ እሰራባቸው ከነበሩ ተቋማት የማገኛቸው ጥቅሞች ተቋርጠውብኛል፣ የዛሬው የፍርድ ቤት ውሳኔም እንባዬን ያበሰ ትክክለኛ ፍትህ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።