ኤለን መስክ ባለፈው ቅዳሜ ለሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ በይፋ ድጋፍ መስጠቱ ይታወሳል
የአለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር ኤለን መስክ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ በየወሩ 45 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ማቀዱ ተነገረ።
ወልስትሪት ጆርናል ምንጭቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ቢሊየነሩ ድጋፉን የሚሰጠው “ፖለቲካል አክሽን ኮሚቴ” (ፒኤሲ) ለተሰኘ ለምርጫ ቅስቀሳ የሚውል ገንዘብን ለሚሰበስብ ተቋም ነው።
መስክ ለፒኤሲ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ብሉምበርግ ባለፈው ሳምንት ቢዘግብም የቴስላና ስፔስኤክስ ስራ አስፈጻሚው "እኔ ለማንኛውም እጩ እንዳልሰጠሁ ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ" ሲል ማስተባበሉ ይታወሳል።
ዶናልድ ትራምፕ ከቀናት በፊት በፔንሲልቫኒያ የምርጫ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው በኋላ ግን የኤክስ (ትዊተር) ባለቤቱ ኤለን መስክ በይፋ ለሪፐብሊካኑ ተወካይ ድጋፍ መስጠቱ አይዘነጋም።
መስክ ለትራምፕ ፕሬዝዳንታዊ እጩነት ድጋፉን በሰጠ ማግስት ለ”ፒኤሲ” በየወሩ 45 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት መወሰኑንና ድጋፉን ከቀጣዩ ሀምሌ ወር ጀምሮ እንደሚጀምር ነው ወልስትሪት ጆርናል ያስነበበው።
ዴሞክራቱ የትራምፕ ተፎካካሪ ጆ ባይደን የአለማችን ቁጥር አንድ ባለጠጋውን “ትዕቢተኛ” ሲሉ የገለጿቸው ሲሆን፥ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድናቸውም መስክ፥ ትራምፕ በድጋሚ ከተመረጠ ታክስ ይቀንስልኛል ብሎ ስለሚያምን ነው ይህን ያደረገው ሲሉ ተደምጠዋል።
ሪፐብሊካኖች ለቴስላ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እውቅና መስጠታቸውም መስክ ለፓርቲው ድጋፍ እንዲሰጥ አድርጎታል ይላሉ።
ዶናልድ ትራምፕ በመጋቢት ወር በፍሎሪዳ በቢሊየነሩ ኔልሰን ፔልዝ መኖሪያ ቤት ኤለን መስክ ጋር ሲገናኙ የኤሌክትሪክ መኪና አድናቂ እንደሆኑ ነግረዋቸው ነበር።
ከፍሎሪዳው የገጽ ለገጽ ግንኙነታቸው በኋላ መስክ በአማካሪነት ወደ ዋይትሃውስ ሊዘልቅ እንደሚችል መነጋሩም የሚታወስ ነው።
ሁለቱ ቢሊየነሮች ግንኙነታቸው እያደገ ሄዶ ትራምፕ ጄዲ ቫንስን ተጣማሪያቸው አድርገው እንዲመርጡ መስክ ግፊት እስከማድረግ መድረሳቸውም ተነግሯል።
በፎርብስ እለታዊ የቢሊየነሮች ደረጃ መሰረት ኤለን መስክ በ252 ቢሊየን ዶላር ቁጥር አንድ የአለማችን ባለጠጋ ነው።