ትራምፕ ከግድያ ሙከራው በኋላ የተገኙበትና ድላቸውን አመላካች ነው የተባለው የሪፐብሊካኖች ጉባኤ
የሪፐብሊካን ፓርቲ ብሄራዊ ጉባኤ ሲጀመር ዶናልድ ትራምፕ በህዳሩ ምርጫ እንዲወዳደሩ በይፋ ተመርጠዋል
ትራምፕ የአንድ ወቅት ተቃዋሚያቸውን ጄዲ ቫንስ የፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተጣማሪያቸው አድርገው መርጠዋቸዋል
የሪፐብሊካን ፓርቲ ሌሊቱን ብሄራዊ ጉባኤውን ሲያደርግ ዶናልድ ትራምፕን በህዳር ወር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲፎካከሩ በይፋ መርጧል።
ከእያንዳንዱ ግዛት የተወከሉ ድምጽ ሰጪዎች ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይሆኑ ዘንድ ድጋፋቸውን በጋለ ስሜት ገልጸውላቸዋል።
ትራምፕ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ከሁለት ቀናት በኋላ በጉባኤው ላይ ሲገኙም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ጉባኤው ተጀምሮ የድምጽ አሰጣጡ እንደቀጠለ ትራምፕ የኦሃዩ ሴናተር የሆኑትን ጄዲ ቫንስ ተጣማሪያቸው (ካሸነፉ ምክትላቸው) እንዲሆኑ እንደመረጧቸው በትሩዝ ሶሻል ማህበራዊ ሚዲያቸው ይፋ አድርገዋል።
በዊስኮንሲን ግዛት ሚልዋኪ እየተካሄደ ያለው ጉባኤ የሪፐብሊካን ፓርቲ ከ2016 ወዲህ በብዙ ረገድ ለውጥ ያሳየበትና ትራምፕ በምርጫው አሸናፊ እንደሚሆኑ አስቀድሞ ያመላከተ ነው ተብሏል።
ተጣማሪያቸው አድርገው የመረጧቸው ጄዲ ቫንስ ምንም እንኳን በትራምፕ ላይ ከዚህ ቀደም ትችት በማንሳት የሚታወቁ ቢሆንም በፓርቲው ውስጥ በርካታ ደጋፊ እንዳላቸው ሬውተርስ ዘግቧል።
የኦሃዩ ተወላጁ ወጣት ሴናተር በተለይ በርካታ ሰራተኛ የሰው ሃይል ባላቸውና ኢንዱስትሪዎች በሚበዙባቸው ግዛቶች ሪፐብሊካኖች ተመራጭ እንዲሆኑ የሚመች ሃሳብ አላቸው ነው የተባለው።
ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዳግም እንዲመለስ ሴት ወይም ጥቁር ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲመርጡ ለጋሾቻቸው ጫና ቢያደርጉባቸውም በ2016 “የአሜሪካው ሂትለር” ያላቸውን የ39 አመቱን ጄዲ ቫንስ መርጠዋል።
ይህም ያለ አጣማሪያቸው ድጋፍ ምርጫውን እንደሚያሸንፉ ሙሉ መተማመናቸውን እንደሚያሳይ ነው ተንታኞች የሚያነሱት።
የ78 አመቱ ትራምፕ በ39 አመት የሚበልጡትን ቫንስ መምረጣቸውም በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወጣቶችን ወደፊት የማምጣት ጥሩ ጅምር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ተገልጿል።
የትራምፕ ምርጫ የቫንስን መመረጥ ባልደገፉ ለጋሾች ዘንድ ተቃውሞም እያስተናገደ ነው።
በ2016 ባሳተመው የግል ህይወቱ ማስታወሻ መጽሃፍ ታዋቂነትን ያተረፈው ጄዲ ቫንስ የ2021ዱን የካፒቶል ሂል ጥቃት በማቅለል ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ግንኙነቱን ማደሱ ይታወሳል።
የየል ዩኒቨርሲቲ ምሩቁ እንደ ኤለን መስክ ካሉ የሲልከን ቫሊ ቢሊየነሮች ጋር ያለው ወዳጅነት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ለምርጫው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻሉም ይነገራል።
አሜሪካ ለዩክሬን የምታደርገው ድጋፍን በመቃውም የሚታወቁት ጄዲ ቫንስ በሪፐብሊካን ፓርቲ ብሄራዊ ጉባኤ ከትራምፕ ጋር ተገኝተዋል።