ዶናልድ ትራምፕ በቀረቡባቸው የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ በመባል የመጀመሪያ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆኑ
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከንግድ ሰነድ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በቀረቡባቸው ሁሉም ክሶች ጥፋተኛ ተብለዋል
ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው የፍርድ ቤት ውሎ 12 ዳኞች የተሳተፉበት ሲሆን የ22 ምስክሮችን ቃል አድምጧል
አወዛጋቢው የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቀረቡባቸው 34 ክሶች በሁሉም ጥፋተኛ ተብለዋል።
ትራምፕ ከንግድ ሰነድ ማጭበርበር ጋር ተያይዞ በቀረቡባቸው ክሶች ከ2016 ጀምሮ በስልጣን ላይ በነበሩባቸው ጊዜያት በእርሳቸው ፊርማ ተፈርመው የወጡ የገንዘብ ሰነዶች እና ቼኮች እንደማስረጃ ቀርበውባቸዋል።
ስቶርሚ ዳንኤልስ የተባለችው የወሲብ ፊልም ተዋናይት ከምርጫው በፊት ከትራምፕ ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት እንደፈጸመች እና ስለዚህ ጉዳይ እንዳታወራም የ130ሺ ዶላር ክፍያ እንደተፈጸመላት በኒውዮርክ ፍርድ ቤት ቀርባ መስክራለች።
የቀድሞ የፕሬዝዳነቱ ጠበቃ ማይክል ኮሀን ይህንኑ ፍርድ ቤት ተገኝተው አረጋገረጠዋል፡፡ ጠበቃው ለዳንኤልስ በትራምፕ አዛዥነት እንዲከፈል የተጠየቀ 130 ሺ ዶላር ክፍያን አስፈጽሚያለሁ ብለዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በኒውዮርኩ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ የተባሉት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ በስልጣን ላይ ያለም ሆነ የቀድሞ ፕቴዝዳነት በወንጀል ጥፋተኛ ሲባል የመጀመርያው ሆነዋል፡፡
ትራምፕ የፍርድ ውሳኔውን የተጭበረበረ እና አሳፋሪ ነው በሚል ሲገልጹት ጠበቆቻቸቸው በበኩላቸው ውሳኔውን እንደማይቀበሉ እና የይግባኝ ጥያቄ ለማቅረብ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ዛሬ ከሰአት ላይ ኒውዮርክ በሚገኝው ትራምፕ ታወር መግለጫ እንደሚሰጡ የሚጠበቁት የቀድሞ ፕሬዝዳንት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ደግሞ የምርጫ ቅስቀሳ ስራቸውን እንደሚቀጥሉ ተነግሯል፡፡
የጥፋተኝነት ውሳኔው በትራምፕ ቀጣይ የፖለቲካ ጉዞ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እስከሁን ግልጽ የሆነ ነገር ባይኖርም የሚያሳድረው ተጽዕኖ ግን ቀላል የማይባል እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ለሀምሌ 11 የመጨረሻ ፍርድ ለመስጠት ቀጠሮ የሰጠው ፍርድ ቤት ውሳኔ የትራምፕን የፖለቲካ ህይወት የሚወስን ነው፡፡ በእርግጥ ፍርድ ቤቱ ጥፈተኛ ናቸው ባላቸው ትራምፕ ላይ የሚያሳልፈው ቅጣት አልታወቀም፡፡
ሮይተርስ ያነጋገገራቸው የህግ ባለሙያዎች ግን የእስር ቅጣት ከአማራጮቹ መካከል ቀዳሚው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
ለዚህም የንግድ ሰነዶችን ማጭበርበር ለአራት አመታት በእስር እንደሚያስቀጣ የሚደነግገውን ህግ በማሳያነት ጠቅሰውታል፡፡
ቀጣይ የትራምፕ ማረፍያ ነጩ ቤተ መንግስት ወይስ በብረት አጥር የተከበበ እስር ቤት የሚለው ከሀምሌ 11 የፍርድ ቤቱ የፍርድ ውሳኔ በኋላ የሚታወቅ ይሆናል፡፡