ትራምፕ የወሲብ ቅሌታቸው እንዲደበቅ ገንዘብ በመክፈል በቀረበባቸው ክስ ፍርድቤት ቀረቡ
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ስቶርም ዳንኤልስ የተባለች የወሲብ ፊልም ተዋናይ ስለነበራቸው ግንኙነት ትንፍሽ እንዳትል 130 ሺህ ዶላር መክፈላቸው ተገልጿል
ትራምፕ በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ከሆኑ እስከ አራት አመት በሚደርስ እስራት ሊቀጡ ይችላሉ ተብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በወሲብ ቅሌት በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ፍርድቤት ቀረቡ።
በወንጀል ክስ ፍርድቤት በመቅረብም በስልጣን ላይ ካሉ ወይንም ከቀድሞ ፕሬዝዳንቶች የመጀመሪያው ሆነዋል ተብሏል።
ትራምፕ በማሃተን ፍርድቤት የቀረቡት በ2006 የወሲብ ፊልም ተዋናይ ለሆነችው ስቶርም ዳንኤልስ በድብቅ ክፍያ ፈጽመዋል በሚል በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በ2016ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ፉክክር በሚያደርጉበት ወቅት ከዳንኤልስ ጋር ፈጽመውታል የተባለው ግንኙነት ከህዝብ እንዲደበቅ 130 ሺህ ዶላር መክፈላቸውንና ለማንም እንዳትናገር ያስፈራሯት እንደነበር ይጠቁማል ክሱ።
የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጠበቃ ማይክል ኮሀን ፍርድ ቤት ቀርቦ በትራምፕ ትዕዛዝ ክፍያውን መፈጸሙን ማመኑም ይታወሳል።
የ77 አመቱ ትራምፕ ግን ከስቶርሚ ዳንኤልስ ጋር ጾታዊ ግንኙነት በጭረሽ አላደረኩም ሲሉ ክሱን ሲያጣጥሉት ቆይተዋል።
ከወሲብ ቅሌት ጋር የተገናኙ ክሶች የተበራከቱባቸው ትራምፕ ክሶቹ ፖለቲካዊ መሆናቸውን በመጥቀስ ደጋፊዎቻቸው እንዲቃወሟቸው ጥሪ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ሬውተርስ አስታውሷል።
ዶናልድ ትራምፕ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ተከትሎ ሁከት ለማስነሳት በመሞከር፣ ሚስጢራዊ መረጃዎችን በማጋራት እና በሌሎች ከአራት በላይ ክሶች የቀረቡባቸው ክሶች በቀጣዩ ምርጫ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ይጠበቃል።
ሬውተርስ ሰበሰብኩት ባለው የህዝብ አስተያየት ከሶስት መራጮች ሁለቱ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የቀረቡ ክሶችን በከፍተኛ አጽንኦት እንደሚመለከቷቸው አሳይቷል።
ትራምፕ በበኩላቸው ክሱቹን በማጣጣል በህዳር ወር 2024 ምርጫ “ካላሸነፍኩ የአሜሪካ ዴሞክራሲ ፍጻሜ ይሆናል” በሚል ከወዲሁ ዛቻ እያሰሙ ነው።
አወዛጋቢው ሰው ከቀረቡባቸው ክሶች ውስጥ ከምርጫው በፊት ብይን ይሰጥበታል ተብሎ የሚጠበቀው ከወሲብ ፊልም ተዋናዩዋ ስቶርም ዳንኤልስ ጋር በተያያዘ የቀረበባቸው የወንጀል ክስ ብቻ ነው ተብሏል።
ትራምፕ በዚህ ክስ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ አራት አመት የሚደርስ እስራት እንደሚጠብቃቸው ቢገለጽም ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ያግዳቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።