የትራምፕ አስተዳደር የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ በቀጣዩ ወር በሩሲያ ጉብኝት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ተገለጸ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝቶ መምከር እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል
ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የዩክሬኑ አቻቸው በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ እንዲታደሙ ሊጋበዙ እንደሚችሉም ተነግሯል
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪት ኬሎግ በሚቀጥለው ወር ኪቭን ከጎበኙ በኋላ ወደ ሞስኮ ለመጓዝ ማቀዳቸውን ብሉምበርግ ጉዳዩን የሚያውቅ ምንጭ በመጥቀስ ዘግቧል።
ምንምእንኳን እቅዱ በውሳኔ ደረጃ ባይጎለብትም ኪሎግ ወደ ሩሲያ የሚያቀኑ ከሆነ የተለየ ፖሊሲ ማስተግበር ላይ ከማተኮር ይልቅ በሞስኮ በኩል የሚነሱ ሀሳቦችን መረጃ በማሰባሰብ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችል ብሎምበርግ አስነብቧል፡፡
ልዩ መልዕክተኛው ወደ ምስራቅ አውሮፓ ከመጓዛቸው በፊት ወደ ለንደን ፣ ፓሪስ እና ሮም በማቅናት በአካባቢው ሁኔታ ዙርያ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
በመጀመሪያው የትራምፕ የስልጣን ዘመን በብሔራዊ ደህንነት ሚናዎች ላይ ያገለገሉት ጡረተኛው ጄኔራል፤ በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል የሰላም ስምምነትን ለማደራደር በመሞከር የወደፊቱ አስተዳደር ቁልፍ ሰው ሆኖው ባለፈው ወር ተሹመዋል፡፡
በብሉምበርግ ዘገባ መሰረት ኬሎግ እና ሌላው የቀድሞ የትራምፕ አማካሪ ፍሬድ ፍሊትዝ ሩሲያ ለተቆጣጠረቻቸው ቦታዎች እውቅና ሳይሰጥ አሁን ባለበት ሁኔት ግጭቱ እንዲቆም የድርድር ሀሳብ ለፕሬዝዳንቱ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሁለቱ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ዙርያ በቅርበት እየሰሩ የሚገኙ አካላት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም የዩክሬንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ማዘግየት እንደሚገባ ምክራቸውን መለገሳቸው ተሰምቷል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ጦርነቱን በ24 ሰአት አስቆማለሁ ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍን በመያዣነት በማቅረብ ኪየቭ ወደ ድርድሩ እንድትቀርብ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችል የዲፕሎማሲ ተንታኞች ያነሳሉ፡፡
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪት ኬሎግ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ደም አፋሳሹን ጦርነት ሊያስቆሙ እንደሚችሉ፤ ፕሬዝዳንት ፑቲን እና የዩክሬኑ አቻቸውን ዘለንስኪን በበዓለ ሲመታቸው ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ሊያቀርቡ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡
በትላንትናው ዕለት ትራምፕ እራሳቸው ጦርነቱን በማስቆም ዙርያ ከዘለንስኪ እና ፑቲን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፑቲን ተመራጩ ፕሬዝዳንት የዩክሬንን ግጭት በማስቆም ላይ የሰጡት መግለጫ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በመጥቀስ ትራምፕን ለማነጋገርም ሆነ አስቀድመው ስልክ ለመደወል እንደማይከብዳቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን ዩክሬን በዘላቂነት የኔቶ አባል እንደማትሆን ማረጋገጫ ማግኘት እና ሩሲያ አሁን የተቆጣጠረቻቸውን ክልሎች እውቅና እንዲሰጥ ክሪምሊን ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ አሁንም አልቀየረም፡፡