ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው ላይ የቻይናው ፕሬዝዳንት እንዲታደሙ ጥሪ አቀረቡ
ከ1874 ጀምሮ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ በዓለ ሲመት ላይ የውጭ ሀገራት መሪዎች ታድመው አያቀኡም
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ባልተለመደ ሁኔታ ከቻይናው አቻቸው በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት መሪዎችን ሊጋብዙ ይችላሉ ተብሏል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቻይናውን ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ በበዓለ ሲመት ፕሮግራማቸው ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡
ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ትራምፕ በህዳ ወር በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በዴሞክራቷ እጩ ካማላ ሃሪስ ላይ ድል መቀዳጀታቸው ከታወቀ በኋላ በጥቂት ጊዜያት ልዩነት ለፕሬዝዳንቱ ግብዣ ማቅረባቸውን ዘግቧል፡፡
በጥር 20 በሚካሄደው ስነስርአት ላይ እንዲታደሙ ጥሪ የቀረበላቸው የቻይናው ፕሬዝዳንት እስካሁን ለግብዣው የሰጡት ምላሽ አልታወቀም፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መዛግብት እንደሚያመለክቱት ከ1874 ጀምሮ ማንም የውጭ ሀገር መሪ በፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ላይ ተገኝቶ አያውቅም ፡፡
እንደ ሲቢኤስ ኒውስ ዘገባ ከሆነ ትራምፕ ባልተለመደ ሁኔታ የሃንጋሪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባንን ጨምሮ ሌሎች የአለም መሪዎችን በስነ ስርዓቱ ላይ ለመጋበዝ አቅደዋል፡፡
ትራምፕ በአዲሱ አስተዳደራቸው በቻይና ላይ ባላቸው ጠንካራ አቋም የሚታወቁ ግለሰቦችን በካቢኔያቸው ውስጥ እያካተቱ ይገኛሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው የታጩት ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ እና በኮንግረሱ የቻይና ፖሊሲዎች እና አካሄዶችን በመተቸት የሚታወቁት የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ተሿሚው ማይክ ዋልዝ ይገኙበታል፡፡
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ወደ ስልጣን ሲመለሱ ከዚህ ቀደም በቻይና ላይ የነበራቸውን ጠንካራ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቀድሞው የፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ትራምፕ የንግድ ጦርነትን ጨምሮ ከቤጂንግ ጋር ከፍተኛ ፍጥጫ ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡
አዲሱ አስተዳደራቸው ደግሞ ከንግድ መብት ጥበቃ እና የአሜሪካውያን ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በሚል ከቻይና በሚገቡ ሸቀጦች ላይ እስከ 60 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ እንደሚያደርግ ዝቷል፡፡
የሀገራቱ ውዝግብ በአዲሱ አስተዳደር ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል እየተሰጋ በሚገኝበት ጊዜ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ታሪክ ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ ትራምፕ በበዓለ ሲመታቸው የቻይናው ፕሬዝዳንት እኒድገኙ አስቀድመው ግብዣ ማቅረባቸው መነጋገርያ ሆኗል፡፡