ትራምፕ በስም ማጥፋት የከሰሱት ኤቢሲ ኒውስ 15 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማማ
የሚዲያ ተቋሙ መጋቢት 10 2024 ላይ በሀሰተኛ መረጃ ትራምፕን መወንጀሉን በመጥቀስ ይቅርታ ጠይቆ ክሱ ይቋረጣል ተብሏል
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይም የ10 ቢሊየን ዶላር ክስ መመስረታቸው ይታወሳል
የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤቢሲ ኒውስ ለተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ 15 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማማ።
የቴሌቪዥን ጣቢያው ገንዘቡን የሚከፍለው በትራምፕ የቀረበበት የስም ማጥፋት ክስ እንዲቋረጥ ነው።
በመጋቢት 10 ቀን 2024 ለትራምፕ ድጋፍ የሰጡ የኮንግስረንስ አባልን ቃለመጠይቅ ያደረገው ጆርጅ ስቴፋኖፑሎስ የሪፐብሊካኑ እጩ በአስገድዶ መድፈር ተጠያቂ ናቸው የሚል ተደጋጋሚ ክስ አቅርቧል።
የትራምፕ ጠበቆችም በትራምፕ ላይ በሀሰተኛ መረጃ ከ10 ጊዜ በላይ ውንጀላ የቀረበበትን ፕሮግራም ያስተላለፈውን ኤቢሲ ኒውስ ከሰዋል።
ፎክስ ኒውስ እንዳስነበበው ኤቢሲ ኒውስ ክሱ እንዲቋረጥ በትራምፕ ለሚቋቋም ፋውንዴሽን 15 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማድረግና እስካሁን ለክስ ሂደት ለወጣው ወጪ 1 ሚሊየን ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል።
በመጋቢት ወር ከተላለፈውና አሁንም በድረገጽ ላይ ከሚገኘው ቪዲዮ ስርም ኤቢሲ ኒውስ እና ጋዜጠኛው ጆርጅ ስቴፋኖፑለስ በይፋ ይቅርታቸውን ያስቀምጣሉ ተብሏል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት "ሀሰተኛ ዜና" አቅራቢ ከሚሏቸው መገናኛ ብዙሃን ጋር ሲፋጠጡ ቆይተዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የቀረቡባቸውን በርካታ ክሶች ያለምንም ማስረጃ እያጎኑ ከፉክክሩ ሊያስወጧቸው እንደጣሩም ያወሳሉ።
በህዳር ወር መጀመሪያም ካማላ ሃሪስን ለማጉላት ያልተገባ የአርትኦት ስራ ሰርቷል ባሉት ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ የ10 ቢሊየን ዶላር ክስ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ትራምፕ በተደጋጋሚ በሀሰተኝነቱ የሚያብጠለጥሉት ሲኤንኤን ከአዶልፍ ሂትለር ጋር አመሳስሎኛል በሚል በ2023 አቅርበውበት የነበረው ክስ ውድቅ ተደርጎባቸው ነበር።
ዋሽንግተንፖስት፣ ኒውዮርክ ታይምስ እና ኤቢሲ ኒውስ ላይም የስማ ማጥፋት ዘመቻ ተከፍቶብኛል የሚሉና ከኢፍትሃዊነት ጋር የተያያዙ ክሶችን ማቅረባቸው አይዘነጋም።