ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝት ሳውዲ አረቢያን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ተናገሩ
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በታሪክ የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ወደ ብሪታንያ ያደርጋሉ
ፕሬዝዳንቱ ሳውዲ አረቢያ የተሻለ ጥቅም ካስገኘች የመጀመሪያ ጉብኝቴን ወደ ሪያድ ላደርግ እችላለሁ ብለዋል
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝት ሳውዲ አረቢያን ሊጎበኙ እንደሚችሉ ተናገሩ።
ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የአሜሪካው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ ከስድስት ቀናት በፊት በይፋ ስልጣን ተረክበዋል።
ከስምንት ዓመት በፊት 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው ቃለ መሀላ ፈጽመው የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣናቸውን ለጆ ባይደን አስረክበው ነበር።
ከአራት ዓመት ዕረፍት በኋላ ዳግም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ነጩ ቤተ መንግሥት ከገቡ በኋላ በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ አዳዲስ ውሳኔዎችን እያስተላለፉ ይገኛሉ።
በእሳት አደጋ እየወደመች ያለችው ካሊፎርኒያ ግዛትን በጎበኙበት ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ የውጭ ሀገር ጉብኝታቸውን ወደ ሳውዲ አረቢያ አልያም ብሪታንያ ሊያደርጉ እንደሚችሉ መናገራቸውን ሮይቱርስ ዘግቧል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች በታሪክ የመጀመሪያ የውጭ ሀገራት ጉብኝታቸውን ወደ ቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው ብሪታንያ ያደርጋሉ።
ይህ ህግ የሻሩት ዶናልድ ትራምፕ ከስምንት ዓመት በፊት ስልጣን በያዙበት ወቅት የመጀመሪያ ጉብኝታቸው ወደ ሪያድ አድርገው ነበር።
አሁንም "የመጀመሪያ ጉብኝቴን ወደ ሳውዲ አረቢያ ላደርግ እችላለሁ" ያሉት ዶናልድ ትራምፕ ሪያድ የተሻለ ጥቅም ለአሜሪካ ካቀረበት እደግመዋለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ሳውዲ አረቢያ ጥሩ የአሜቲካ ወዳጅ ነች ብለው እንደሚያስቡም ተገልጿል።
ከአራት የዕረፍት ዓመታት በኋላ ወደ ነጩ ቤተመንግስት የተመለሱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቀድሞ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተወሰኑ ውሳኔዎችን በመሻር ላይ ናቸው።
በስደተኞችን ላይ የከረረ አቋም ያላቸው ትራምፕ ከወዲሁ ከ500 በላይ ስደተኞችን በግዳጅ ወደየመጡበት ሀገራት መልሰዋል።
በቀጣይም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በግዳጅ እንደሚመልሱ የሚጠበቅ ሲሆን ጉዳዩም ከወዲሁ በአሜሪካ ዋነኛ አጀንዳ ሆኗል።