ትራምፕ በአሜሪካ የሚወለዱ ህጻናት በቀጥታ ዜግነት እንዳያገኙ ያሳለፉት ውሳኔ በፌደራል ዳኛ ታገደ
22 ግዛቶች ህጻናትን "ሀገር አልባ" ያደርጋል ያሉት የፕሬዝዳንቱ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ እንዲታገድ ክስ መስርተዋል
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሲያትል በሚገኙት የፌደራል ዳኛ የተላለፈውን ውሳኔ ለማሻር ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሚወለዱ ህጻናት በቀጥታ የሀገሪቱ ዜግነት ማግኘት የሚፈቅደውን ህግ ከቀናት በፊት በፈረሙት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ሽረዋል።
ስደተኞች የአሜሪካዊያንን ጥቅም እየጎዱ ነው የሚል አቋም ያላቸው ትራምፕ፥ አሜሪካዊ ልጆች ያሏቸውንም ወላጆች አብሬ ወደመጡበት አባርራለሁ ማለታቸው ተቃውሞ አስነስቶባቸዋል።
ትራምፕ ዋይትሃውስ እንደገቡ የፈረሙት የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ከህገወጥ ስደተኞች ተወልደው የአሜሪካ ዜግነት ያገኙ ህጻናት ከየካቲት 19 2025 ጀምሮ እንደ ዜጋ አይቆጠሩም ይላል።
ትዕዛዙ አሜሪካ በህጋዊ መንገድ ከገቡ እናቶች (ለጉብኝት፣ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት እና ጊዜያዊ ስራ) የተወለዱ ህጻናት አባታቸው አሜሪካዊ ዜጋ ካልሆነ በስተቀው የሀገሪቱ ዜጋ እንደማይሆኑም ይጠቅሳል።
22 ግዛቶች ውሳኔው ህጻናትን "ሀገር አልባ" ያደርጋል በሚል ስድስት ክሶችን መስርተዋል።
በሲያትል የሚገኘው የፌደራል ፍርድቤት ዳኛ ጆን ኮግሄኑር በዋሽንግተን አቃቤ ህግ ኒክ ብራውን እና በሶስት ግዛቶች (አሪዞና፣ ኢሊኖይስ እና ኦሪገን) የቀረበውን የትራምፕ የስራ አስፈጻሚ ትዕዛዝ ይታገድ ጥያቄ ተመልክተዋል።
ዳኛው ውሳኔው "ኢህገመንግስታዊ" ነው በሚል ለ14 ቀናት እንዲታገድና ቀኑ ሲጠናቀቅ እንዲራዘም መወሰናቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስነብቧል።
ትራምፕ የዳኛውን ውሳኔ ተከትሎ በዋይትሃውስ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ "ይግባኝ እንጠይቃለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የትራምፕ ውሳኔ በአሜሪካ በየአመቱ የሚወለዱ ከ150 ሺህ በላይ ህጻናትን መብትና ጥቅሞች የሚያሳጣ ነው ተብሏል፤ የተወሰኑትንም ሀገር አልባ ያደርጋል በሚል አራት ግዛቶች ባለ32 ገጽ ቅሬታ አቅርበዋል።
18 ግዛቶች ውሳኔው እንዲሻር ያቀረቡት ክስ በማሳቹሴትስ በሚገኝ ፍርድቤት ይታያል።
ነፍሰጡር እናቶች እና የመብት ተሟጋቾች ያቀረቧቸው ክሶችም በሜሪላንድ፣ ማሳቹሴትስ፣ ኒው ሃምፕሻየር እና ካሊፎርኒያ እንደሚታዩ ሲኤንኤን አስነብቧል።
ክሶቹ የአሜሪካ ህገመንግስት በ14ኛ ማሻሻያው የሰጠውን መብት (በአሜሪካ አፈር የተወለደ ህጻን ሁሉ ዜግነት ያገኛል) የሚጥስ መሆኑን የሚገልጹና የትራምፕ ውሳኔ በፍጥነት እንዲታገድ የሚጠይቁ ናቸው።