ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆም ከፑቲን ጋር "በፍጥነት" መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጹ
ፕሬዝደንት ትራምፕ ምርጫ 2024ን እስከሚያሸንፉበት ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ቢሮ በገቡበት ቀን ሩሲያና ዩክሬንን እንደሚያስማሙ ሲገልጹ ቆይተዋል
ትራምፕ በዳቮስ ለተገኙ ተሳታፊዎች አሜሪካ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ በተስፋ እየሰራች ነው ብለዋል
የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለማስቆም በተቻለ ፍጥነት የሩሲያውን ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንን አግኝተው ማናገር እንደሚፈልጉ በትናንትናው ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ምርጫ 2024ን እስከሚያሸንፉበት ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ቢሮ በገቡበት ቀን ሩሲያና ዩክሬንን እንደሚያስማሙ ሲገልጹ ቆይተዋል። አሁን ላይ አማካሪዎቻቸው ጦርነቱን ማስቆም ወራትን እንደሚወስድ አምነዋል።
"ጦርነቱ እንዲቆም ፕሬዝደንት ፑቲንን በቅርቡ ማግኘት እፈለረጋለሁ" ሲሉ ባለፈው ሰኞ ወደ ኃይትሀወስ የገቡት ትራምፕ ዳቮስ በተካሄደው የአለም የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ በቪዲዮ ሊንክ ተናግረዋል።
"ይህ ከኢኮኖሚ ወይም ከሌላ አንጻር አይደለም። እየባከነ ካለው በሚሊዮን የሚቆጠር የሰው ህይወት አንጻር ነው የሚታየው። እልቂት ነው፤ ማስቆም አለብን።"
ትራምፕ ቆየት ብለው በእለቱ በኃይትሀውስ በሰጡት መግለጫ አላስፈላጊ ነው ያሉትን ጦርነት ለማስቆም በተቻለ ፍጥነት ፑቲንን ለማግኘት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"እንደምሰማው ከሆነ ፑተን እኔን ማግኘት ይፈልጋል። በተቻለ ፍጥነት ለመገናኘት እንሞክራለን። በፍጥነት አገኘዋለሁ" ብለዋል ትራምፕ።
"ባልተገናኘንበት በእያንዳንዱ ቀን በጦር ሜዳ ወታደሮች እየተገደሉ ነው" ያሉት ትራምፕ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ ጦርነቱ እንዲቆም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውን እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
ትራምፕ በዳቮስ ለተገኙ ተሳታፊዎች አሜሪካ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲገኝ በተስፋ እየሰራች ነው ብለዋል። ነገርግን ትራምፕ ዝርዝር ጉዳዮችን ይፋ አላደረጉም።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ትራምፕ ሩሲያ ጦርነቱን ለማቆም የማትስማማ ከሆነ ከፍተኛ ማዕቀብ እንደሚጥሉና ከሞስኮ በሚገቡ እቃዎች ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ አስጠንቅቀው ነበር።
የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ እንዲደረግ እንደሚፈልጉ በስብሰባው ላይ የተናገሩት ትራምፕ ሩሲያና ቻይና የኑክሌር አቅማቸውን በመቀነስ ሀሳብ ሊስማሙ ይችላሉ ብለዋል።
"የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ እንዲኖር እንፈልጋለን...ፕሬዝደንት ፑቲን የኑክሌር ጦር መሳሪያ ቅነሳ የሚለውን ሀሳብ በእውነት እንደምወደው እነግርሃለሁ። የተቀረው አለም እንዲሁም ቻይና ትከተላለች ብዮ አስባለሁ" ብለዋል ትራምፕ።
ፕሬዝደንት ፑቲን በዩክሬኑ ጦርነት የኑክሌር ጦር መሳሪያ ሊጠቀሙ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል። ፑቲን የአሜሪካ-ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ገደብ ቁጥጥር ስምምነት በ2026 ከተጠናቀቀ በኋላ በድጋሚ ከዋሽንግተን ጋር ለመነጋገር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።