በዶናልድ ትራምፕ ምክንያት የአሜሪካ ዲሞክራሲ እየተጎዳ መሆኑን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መናገራቸው ይታወሳል
አሜሪንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 ድረስ ባሉት አራት ዓመታት ውስጥ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዶናልድ ትራምፕ በጆ ባይደን ተሸንፈው ከፕሬዝዳንትነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ዳግም ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥተዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ትራምፕ በሚቀጥለው ሳምንት በሚካሄደው የህግ አውጪዎች ምክር ቤት ምርጫ ለሪፐብሊካን ፓርቲ ባደረገው ቅስቀሳ ላይ እንዳለው ይህ ዓመት ወደ ነጩ ቤተመንግስት ለመመለስ እርምጃ የምንጀምርበት ወቅት ነው ብሏል፡፡
ትራምፕ አክለውም በዚህ ዓመት የሚካሄደው ምርጫ አብላጫውን የሴኔት መቀመጫዎችንእንቆጣጠራለን ከዚያ ደግሞ በ2024 የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዳግም እናሸንፋለን ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፓርቲያቸውን ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ለሚወዳደሩ ፖለቲከኞች የምረጡኝ ቅስቀሳቸውን አድርገዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ፓርቲያቸው በካሊፎርኒያ ባዘጋጀው የመጨረሻ ቅስቀሳ ፕሮግራም ላይ እንዳሉት ሪፐብሊካኖች የምርጫ ውጤት በመካድ እንደሚታወቁ ገልጸው በ2020 የተደረገውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለአብነት አንስተዋል፡፡
ዲሞክራሲ ያለው በድምጽ መስጫ ኮሮጆ ውስጥ ነው፣ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ የመራጮችን ድምጽ አለማክበር አሜሪካንን ለአስርት ዓመታት ወደኋላ ይጎትታል ሲሉም አክለዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ባይደን ላለፉት አራት ቀናት በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች ተዘዋውረው የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉ ሲሆን ፔንሲልቫኒያ፣ ኒው ሜክሲኮ፣ ኢሊኖይስ እና ካሊፎርኒያ ደግሞ ቅስቀሳ ያደረጉባቸው ግዛቶች ናቸው፡፡
በአሜሪካ የመካከለኛ ዘመን ምክር ቤት ምርጫ ታሪክ ፕሬዝዳንቱ ያለበት ፓርቲ በምርጫው አብላጫ የሚወሰድበት ሲሆን ዘንድሮም የፕሬዝዳንት ጆ ባይደኑ ዲሞክራት ፓርቲ አብላጫ እንዳይወሰድበት ተሰግቷል፡፡
በዚህ ምርጫ ላይ ሪፐብሊካኖች የኮንግረሱን አብላጫ ወንበር የሚቆጣጠሩ ከሆነ ፕሬዝዳንት ባይደን ቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ከባድ ጊዜ ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡በዶናልድ ትራምፕ ምክንያት የአሜሪካ ዲሞክራሲ እየተጎዳ መሆኑን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መናገራቸው ይታወሳል