ትኬት የሌላቸው ደጋፊዎች የ2022 የዓለም ዋንጫ አስተናጋጇ ኳታር መግባት እንደሚችሉ ተገለፀ
የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ከህዳር 11 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳል
ወደ ኳታር ለመግባት የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ውጤትና የክትባት ማረጋገጫ አያስፈልግም ተብሏል
የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን በዓለም ዋንጫው ወቅት የስታዲየም መግቢያ ትኬት ሳይይዙ ወደ ኳታር መጓዝ እንደሚችሉ የኳታር የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ፤ የ2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ የኳታር የምድም የደረጃ ጨዋታ ካለቀ በኋላ በፈረንጆቹ ከታህሳስ 2 2022 ጀምሮ ትኬት የሌላቸው ደጋፊዎች ወደ ኳታር ግዛት መግባት እንደሚችሉ ስናበስር በጣም ደስ እያለን ነው ብሏል።
በዚህም መስረት በዚህ የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ወቅት በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኝ የእግር ኳስ አፍቃሪ ወደ ኳታር በመጓዝ በሳቢውን የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ ድባብ ላይ መካፈል እንደሚችል ተነግሯል።
ወደ ኳታር ለመጓዝ የሚፈልጉ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ወደ ሀገሪቱ እንዲሁም የዓለም ዋንጫ ወደ የሚካሄድባባቸው ስታዲየሞች ለመግባ አስፈላጊ ለሆነው “ሃያ ካርድ” ማመልከት አለባቸው ተብሏል።
ማመልከት የሚፈልጉ ሰዎች በኳታር 2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ድረ ገጽ ወይም “ሃያኳታር 22” የሞባይል መተግበሪያ በኩል ማመልከት እንደሚችሉም ተነግሯል።
“ሃያ ካርድ”፤ የደጋፊ መታወቂያ የያዙ ሰዎች በኳታር ቆይታቸው የሜትሮ እና የአውቶቡስን ጨምሮ ሌሎች የትራንስፖርት አገልግሎቶችን በነጻ ያገኛሉ ተብሏል።
በተጨማሪም “ሃያ ካርድ” የያዙ ሰዎች በኳታር በፈረንጆቹ እስከ ጥር 23፣ 2023 ድረስ መቆየት እንደሚችሉም ታውቋል።
ተጓዦች ወደ ኳታር ለመግባት የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት ማቅረብ አያስፈልጋቸውም የተባለ ሲሆን፤ ኳታር ለመግባት የኮቪድ ክትባት ሰርተፍኬት እንደማያስፈልግም ተገልጿል።
የ2022 የኳታር የዓለም ዋንጫ ከህዳር 11 ቀን 2015 ዓ.ም እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።